Wednesday, September 24, 2014

በሐሰተኛ ማዕረግ ማጭበርበር በመፈጸም የተጠረጠሩት አቶ ሳሙኤል ዘሚካኤል ክስ ተመሠረተባቸው



-  ተታልያለሁ በማለት የቀረቡት የአምባሳደር ልብስ ስፌት ባለቤት ብቻ ናቸው

‹‹ዶ/ር ኢንጂነር ነኝ›› በሚል ሐሰተኛ ማዕረግ በመጠቀም የማታለል ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ተጠርጥረው በእስር ላይ በሚገኙት አቶ ሳሙኤል ዘሚካኤል ላይ፣ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ መስከረም 12 ቀን 2007 ዓ.ም. ክስ መሠረተ፡፡

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት (ሰባራ ባቡር አካባቢ በሚገኘው ፍርድ ቤት) ክስ በተመሠረተባቸው አቶ ሳሙኤል ላይ ‹‹ተታልያለሁ ወይም ተጭበርብሬያለሁ›› በማለት ቀርበው ቃል የሰጡት፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 14 ገርጂ የሚገኘው አምባሳደር ልብስ ስፌት ባለቤት አቶ ሰዒድ መሐመድ ብቻ መሆናቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ጳጉሜን 4 ቀን 2006 ዓ.ም. ጽፎ መስከረም 6 ቀን 2007 ዓ.ም. በፍርድ ቤት የክስ ፋይል የከፈተበትና መስከረም 12 ቀን 2007 ዓ.ም. ተጠርጣሪው ፍርድ ቤት የቀረቡበት ክስ እንደሚያስረዳው፣ አቶ ሳሙኤል የካቲት 12 ቀን 2004 ዓ.ም. ከጠዋቱ 5፡00 ሰዓት ወደ አምባሳደር ልብስ ስፌት ፋብሪካ ይሄዳሉ፡፡ ራሳቸውን ‹‹ዶ/ር ኢንጂነር›› በማለት ሐሰተኛ ማዕረግ በመናገርና ማንነታቸውን በመሰወር፣ ስለሚሠሩት ሥራ ማስተዋወቃቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡


የልብስ ስፌት ፋብሪካውን ባለቤት አቶ ሰዒድን፣ ‹‹ድርጅትህን በተለያዩ መድረኮች አስተዋውቃለሁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የ20 ሰዎች የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ስለምጽፍ በመጽሐፉ ላይ ድርጅትህን አስተዋውቃለሁ፤›› በማለት 58,956 ብር ከ52 ሳንቲም በቼክ ቁጥር 0998563 እንዲሰጧቸው በማድረግ በማታለል መውሰዳቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

ሁለተኛ ክስ ሆኖ በዓቃቤ ሕግ የቀረበው ድርጊት አቶ ሳሙኤል በዚያው በአምባሳደር ልብስ ስፌት ፋብሪካ የካቲት 24 ቀን 2006 ዓ.ም. ተገኝተው፣ ‹‹ዶ/ር ኢንጂነር ነኝ›› በማለት ማንነታቸውን ደብቀውና በሐሰተኛ ማዕረግ ተጠቅመው ‹‹ተማሪዎችን አሠለጥናለሁ፡፡ የማሠለጥናቸውን ተማሪዎች እሸልማለሁ፤›› በማለት 6,799 ብር ከ54 ሳንቲም ግምት ያላቸው የተለያዩ አራት ሙሉ ልብሶችን በመውሰድ የማታለል ወንጀል መፈጸማቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡

ሌላው ተጠርጣሪው መጋቢት 11 ቀን 2006 ዓ.ም. በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ልዩ ቦታው ቲኬ ሕንፃ ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቻይና አፍሪካ አደባባይ ቅርንጫፍ በመገኘት፣ ከባንኩ ገንዘብ ለመበደር የንግድ ፈቃድ ያስገባሉ፡፡ በ2003 ዓ.ም. ከየካ ክፍለ ከተማ ‹‹ቤቴል ሜዲካል ኮሙዩኒኬሽን ኤንድ ኮንሰልታንሲ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር›› በሚል የተሰጣቸውንና የ2004 ዓ.ም.፣ የ2005 ዓ.ም. እና የ2006 ዓ.ም. ላይ ዓመተ ምሕረቶቹን በእጃቸው በመጻፍ፣ በመፈረምና ሐሰተኛ ማህተም በመምታት ያቀረቡ በመሆናቸው ሐሰተኛ ሰነድ በመገልገል ወንጀል መከሰሳቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

አቶ ሳሙኤል መስከረም 12 ቀን 2007 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው ክሱ ከተሰጣቸው በኋላ፣ ከጠበቃ ጋር እንዲቀርቡና የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች በመጥሪያ እንዲቀርቡ ፍርድ ቤቱ በማዘዝ፣ ክስ ለመስማት ለመስከረም 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ግለሰቡ በተጠረጠሩበትና በተከሰሱበት የወንጀል ሕግ ቁጥር 692(1) መሠረት ጥፋተኛ ሆነው ቢገኙ፣ በቀላል እስራት ማለትም ከአሥር ቀናት እስከ ሦስት ዓመታት ወይም እንደ ወንጀሉ ክብደት ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራትና ከአሥር ብር እስከ 10,000 ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ሊጣልባቸው ይችላል፡፡

እንዲሁም በወንጀል ሕግ አንቀጽ 378 መሠረት ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ፣ ከሦስት ወራት በማያንስ ቀላል እስራት ወይም ወንጀሉ በጣም ከባድ ሆኖ ከተገኘ ከአሥር ዓመታት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ሊቀጡ ይችላሉ፡፡

አቶ ሳሙኤል ‹‹ዶ/ር ኢንጂነር›› የሚለው ማዕረግ እንደሌላቸው በመገናኛ ብዙኃን ከተገለጸ በኋላ ምንም ዓይነት ምላሽ ሳይሰጡ ድምፃቸውን አጥፍተው ወደ ኬንያ የሄዱ ቢሆንም፣ በኬንያ የፀጥታ ኃይሎች ተይዘው ለአንድ ሳምንት ከታሰሩ በኋላ ሁለቱ አገሮች ባላቸው ስምምነት መሠረት ሐምሌ 22 ቀን 2006 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ መንግሥት ተላልፈው መሰጠታቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ተጠርጣሪው ሐሰተኛ የማዕረግ ስም መጠቀማቸው በመገናኛ ብዙኃን በተነገረበት ወቅት በርካታ ግለሰቦች በመገናኛ ብዙኃን እየቀረቡና ስልክ እየደወሉ፣ የተለያዩ ማጭበርበሮች እንደተፈጸመባቸው ማለትም ገንዘብ፣ ኮምፒዩተርና ሌሎችንም እንደተጭበረበሩ የገለጹ ቢሆንም፣ ከአምባሳደር ልብስ ስፌት ባለቤት ከአቶ ሰዒድ መሐመድ በስተቀር በክሱ የተጠቀሰ የግል ተበዳይ የለም፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment