Sunday, September 7, 2014

መምህር ሲወድቅ




ተወልዳ ያደገችው፤ትምህርት የጀመረችው ከአዲስ አበባ ሰባት መቶ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በምትገኝ ከተማ ነው፡፡ ቤተሰቦቿን፤ ጓደኞቿንና የትውልድ ቀዬዋን ጥላ ከኮበለለች አራት አመታት አለፉ፡፡ለስደት እግሯን ስታነሳ የትውልድ ቀዬዋን  መለስ ብላ የምታይበት ወኔ እንኳ አልነበራትም፡፡ስምረት(ስሟ የተቀየረ) የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሳለች መምህሯ ቀረባት፡፡ "ቆንጆ ነሽ አለኝ፡፡ስለ ቁንጅናዬ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ወንድ ልጅ ስለ ቁንጅናዬ ሲነግረኝ የመጀመሪያዬ ስለነበር ቀን ከሌት ስለ መምህሬ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ወጣት ነው፡፡ጎበዝ ተማሪ ባልሆንም ምርጡ መምህሬ አድርጌ እቆጥረው ጀመር፡፡ወደ ክፍል ሲገባ አይን አይኑን አየዋለሁ፡፡አይን ለአይን ከተያየን የምገባበት ይጠፋኛል፡፡" ስትል ለመምህሯ ያደረባትን ስሜት ታስታውሳለች፡፡እንዲህ በበጎ ቀልቧን የሰረቀው መምህር ግን ለህይወቷ መኮላሸት ምክንያት ይሆናል ብላ አላሰበችም፡፡እናም ቀረበቸው፡፡በተለያዩ ቀናት የጋበዛትን ሻይ ጠጣች፡፡ሲነካካት ብትሽኮረመምም ተፍነከነከች፡፡ከንፈሮቿን ሲስም እንደወደዳት አመነች፡፡እርሷም እንደ ወደደችው ታውቅ ነበር፡፡አድርጊ ያላትን ሁሉ አደረገች፡፡ቀድሞም በቅጡ የማትከታተለውን ትምህርት ችላ አለችው፡፡ሃሳቧ ሁሉ በመምህሯ ተሸነፈ፡፡ ይህን እየተናገረች ፊቷ ቅጭም አለ፡፡አይኖቿ  እንባ አቀረሩ፡፡ከመምህሯ ጋር የጀመረችው ወዳጅነት እንደአጀማመሩ እንዳልቀጠለ ይህ ስሜቷ ያሳብቃል፡፡

ሃሳባዊው መስመር (Conceptual framework)

የመምህር -ተማሪ የርስ በርስ ግንኙነት ለመማር-ማስተማር ሂደት ውጤታማነት የማዕዘን ድንጋይ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ግንኙነቱ ምቹ የትምህርት ቤትና የመማሪያ ክፍል ለመፍጠር፤ የተማሪዎችን የመማር ፍላጎት ለማሳደግ እና ስኬታማነታቸውን ለማመቻቸት መልካም መሆን ይኖርበታል፡፡ ለሚፈለገው ውጤታማነት የግንኙነቱን ድንበር (ስምረትና መምህሯን ልብ በሉ) መፈተሽና ማረቅ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ አገልጋይንና ተገልጋይን በሚያገናኙ ሙያዎች ውስጥ (Helping Professions) የሁለቱ ወገኖች የርስ በርስ የግንኙነት ድንበር  በስነ-ምግባር ህግጋት (codes of conduct) ይበየናል፡፡( Holmes, Rupert, Ross, & Shapera, 1999; Reamer, 2003; Wright, 2004). የስነ-ምግባር ህግጋቱ የግንኙነቱን ተገቢነትና ኢ-ተገቢነት ከመወሰን ባሻገር ማስገደድ፤ማገድና መወሰን ይችላሉ፡፡They ‘‘act to constrain, constrict, and limit’’ (Austin, Bergum, Nuttgens, & Peternelj-Taylor, 2006, pp. 77–78). በመማር-ማስተማር ሂደት ውስጥ ግን የስነ-ምግባር ህግጋት ገዢነት ሁሌም ስኬታማ  አይሆንም (Andrzejewski & Davis, 2008)፡፡እንዲያውም በመምህር-ተማሪ ግንኙነት ውስጥ የስነ-ምግባር ድንበርን የተመለከቱ ጉዳዮች (Ethical Boundary Issues) በአግባቡ አለመፈተሻቸውን በዘረፉ አንቱ የተባሉ ምሁራን ፅፈዋል፡፡መምህርና ተማሪ የሚኖራቸው የአብሮነት ቆይታ፤የሚያልፉበት የስሜት ልምድ (Emotional Experience) እና የእድገት ሂደት እንደሌሎች ሙያዎች ግንኙነታቸውን በስነ-ምግባር ህግጋት ለመወሰን ፈተና ይሆናሉ፡፡


መምህር ሲወድቅ
የኛ ሙሽራ ኩሪ ኩሪ
ወሰደሽ አስተማሪ

በኢትዮጵያ ታሪክ መምህር መሆን ብርቅ በነበረበት ዘመን ከእነርሱ ጋር ሶስት ጉልቻ መመስረት በማህበረሰቡ ተቀባይነት ነበረው፡፡በሂደት ግን ቤተሰብ፤ማህበረሰብ እና ሃገር አምነው ልጆቻቸውን የሰጧቸው መምህራን በእውቀት፤በስነ-ምግባር እና ቁርጠኝነት (Commitment) መውደቃቸው ዘርፉ የገጠመው ፈተና ሆኗል፡፡በተለይ በስነ-ምግባር የወደቁ መምህራን  የኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎችን ቁም ስቅል እያሳዩ መሆኑን ከሃሜት በዘለለ በርካቶች በመማረር ይናገራሉ፡፡ከጥራት ይልቅ ለሽፋን ትኩረት የሰጠውና በባለሙያዎች ለሚሰጠው ትችት ጆሮ ዳባ ልበስ ያለው ኢህአዴግ መራሹ መንግስት በዘርፉ የሚሾማቸው የትምህርት መሪዎች ከብቃት ይልቅ ለታማኝነት ቅድሚያ የሚሰጡ ናቸው፡፡የትምህርት አመራሮቹ በእውቀት፤ብቃትና ሃላፊነት ሃገርና ትውልድን ከመምራት ይልቅ ʻካርዷʼን ተከታዮች ይበዛሉ ሲሉ የኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓትና የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ ላይ የሚብሰለሰሉ ይተቻሉ፡፡የትምህርት መሪዎች(Educational leaders) ለተማሪዎቻቸው፤ለወላጆች፤ለትምህርት ቤታቸው፤ለማህበረሰቡና በአጠቃላይ ሃላፊነት አለባቸው ሲል ስታራት(2004) የተባለ አሜሪካዊ የስነ-ትምህርት ባለሙያ ያስረዳል፡፡ዛሬ በሆቴል አስተናጋጅነት ህይወቷን የምትገፋው ስምረት የገጠማት እርሷ፤ቤተሰቦቿ፤ትምህርት ቤቱ እና ማህበረሰቡ የሰጡትን ሃላፊነት የዘነጋ በስነ-ምግባርም የወደቀ መምህር ነበር፡፡
“ቤቱ እየወሰደ ይስመኝ እንደሚወደኝም ይነግረኝ ነበር፡፡ብዙ ቀናት ሴክስ እንድናደርግ ቢጠይቀኝም እምቢ እያልኩ አቆይቼዋለሁ፡፡የዛን ቀን ግን 'ዛሬ ሴክስ ካላደረግን አትወጂኝም ማለት ነው' አለኝ፡፡ስለምወደው ሃሳቡን ፈራሁ፡፡ጥሎኝ የሚሄድ መሰለኝ፡፡እሺም እምቢም ሳልለው ልብሴን ማወላለቅ ጀመረ፡፡እጅግ ግራ ስለተጋባሁ አላስቆምኩትም፡፡ሲያመኝ እያደረግን እንደሆነ ገባኝ፡፡” ስትል የትናንት ታሪኳን ታወጋለች፡፡ ይህ ሲሆን ስምረት የመደራደር አቅም (Bargaining Power) አልነበራትም፡፡ ሁለቱም የፍቅር ግንኙነታቸው ያለበትን ደረጃ የመፈተሽ እድል አልነበራቸውም፡፡

መምህራን ከተማሪዎቻቸው ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው ባለሙያዎችና ግንኙነታቸውን ለመደንገግ የተበጁ የስነ-ምግባር መርሆች ይመክራሉ፡፡በትምህርት ቤት፤ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ወጣት ተማሪዎች በስሜት፤በአካልና ስነ-ልቦና የሚያልፉበት የእድገት/የለውጥ ሂደት ከመምህራኖቻቸው ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ላይ አዎንታዊ/አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳርፋል፡፡መምህራኑ  በዚህ የእድገት/የለውጥ ሂደት  ውስጥ ካሉት ተማሪዎቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት መቆጣጠር ከተሳናቸው የተጣለባቸውን ሃላፊነት የሚፈታተን ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ከአሜሪካን ግዛቶች አንዷ በሆነችው ኢዳሆ ለመምህራን የወጣ የስነ-ምግባር መርህ ይህን አላስፈላጊ ግንኙነት ላለመፍጠር መምህራን ከተማሪዎቻቸው ጋር በት/ቤትም ይሁን ከት/ቤት ውጪ አንድ ለአንድ ከመገናኘት እንዲታቀቡ፤በተማሪዎቻቸው የግል ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡ፤ወሲባዊ ፍላጎትን በሚጠቁም መንገድ እንዳይነካኩ ይመክራል፡፡ፍላጎቱ ከተማሪዎች ከመጣም መምህራን በፍጥነት ለትምህርት ቤቱ አስተዳደር ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡መምህራን ተማሪዎቻቸው በመኖሪያ ቤታቸው እንዲገኙ መፍቀድና የአልኮል መጠጥ በሚቀርብባቸው ማህበራዊ ግንኙነቶች በአንድነት መታደምም በኢዳሆ አይፈቀድም፡፡
እንደ የትምህርት መሪ የሚቆጠሩት መምህራን ከተጣለባቸው ሃላፊነት አንፃር ሁሌም የተማሪዎቻቸው፤ወላጆችና አጠቃላይ ማህበረሰቡ ክትትል አይለያቸውም፡፡ለዚህም በአለባበሳቸው፤አመጋገባቸው፤ከሌሎች ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡መምህራን ለተማሪዎቻቸው አርአያ በመሆናቸውና ማህበረሰቡ/ሃገር ከጣለባቸው ሃላፊነት አንፃር ሙያዊ ማንነታቸውን  ከግለሰባዊነታቸው መነጠል የሚሆን አይደለም፡፡
ስምረት ከመምህሯ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ወሲባዊ ግንኙነት ከፈፀመች በኋላ ወዳጅነታቸው እንደ ቀድሞው አልቀጠለም፡፡


"ከዛ በኋላ አንድ ሶስት ቀን ሻይ ጠጣን፡፡ቀስ እያለ ጠፋ፡፡ራቀ፡፡ግራ ገባኝ፡፡የእሱ መራቅ ሳያንስ ፔሬዴ ሳይመጣ ቀረ፡፡ደነገጥኩ፡፡ለጓደኛዬ አማክሪያት እንድመረመር ወሰንን እናም እርጉዝ ሆኜ ተገኘሁ፡፡" ትላለች፡፡በተደራጀ ጥናታዊ ፅሁፍ ማስደገፍ ባይቻልም እንደ ስምረት ሁሉ ከተማሪዎቻቸው ጋር የፍቅርና/የወሲብ ግንኙነት የመሰረቱ መምህራን ቁጥር ጥቂት አይደለም፡፡በተለይ ወጣት ወንድ መምህራን የፈለጓቸውን እንስት ተማሪዎች ከእጃቸው ማስገባት ቀላል እንደሆነ ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ከተማሪዎቻቸው ጋር ባላቸው ወሲባዊ ግንኙነት እርስ በርስ ሲፎካከሩ አንዷን በሌላ ሲቀይሩ የተመለከቱ አንድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር “ጉዳዩን ለትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ባሳውቅም እንደ ግለሰብ በሁኔታው ከመደናገጥና ከማዘን ባሻገር ዘላቂ የመፍትሄ እርምጃ አልተወሰደም፡፡” ሲሉ ይማረራሉ፡፡ስማቸውና የሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት ይቆይ ያሉ ሁለት እንስት መምህራን በበኩላቸው ወጣት መምህራኑ ጉዳዩን በጀብደኝነት ሲያወሩት አንዳች ሃፍረት ወይም የጥፋተኝነት ስሜት እንደማይሰማቸው ፤በትምህርታቸው ቸልተኛ በውጤታቸውም ደካማ የሆኑ እንስት ተማሪዎች ለእነዚህ መምህራን ወጥመድ ቅርብ መሆናቸውን ፤ጉዳዩ ጥፋት ሆኖ ሲገኝም የትምህርት ቤት አስተዳደሮች ከቅያሬ የዘለለ እርምጃ እንደማይወሰዱም ይናገራሉ፡፡ የስምረትን አስከፊ የሚያደርገው የገጠማትን አላስፈላጊ እርግዝና ተከትሎ በህይወቷ የተፈጠረው ዝብርቅርቅ ነው፡፡ስምረት 11ኛ ክፍል የደረሰች ቢሆንም ራሷን የምትጠብቅበት የስነ-ተዋልዶ ጤና እውቀት አልነበራትም፡፡ቢኖራትም አላዳናትም፡፡የነበራት አማራጭ ጉዳዩን ለወዳጅና መምህሯ መናገር ስለ ነበር ወደ ቤቱ አዘገመች፡፡ "ምርጫ ስላልነበረኝ ልነግረው ወደቤቱ ሄድኩ፡፡አንገቱን ብቻ ወጣ አድርጎ አየኝና ምን እንደምፈልግ ጠየቀኝ፡፡ማርገዜን ነገርኩት፡፡ደንግጦ በሩን ሲከፍተው አልጋው ላይ ትምህርት ቤት የማውቃት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ተቀምጣ ነበር፡፡"  መምህሯ ስምረት፤ቤተሰቦቿና ሃገር ከሰጡት ሃላፊነት ወድቋል፡፡ቤተሰቦቿን አብዝታ በመፍራቷ ከጓደኞቿ በተበደረችው ገንዘብ የትውልድ ቀዬዋን ተሰናበተች፡፡ስምረት አዲስ አበባ ከገባች በኋላ የሁለት ወሩን እርግዝና በባህላዊ መንገድ ለማስወረድ ሙከራ አድርጋ ነበር፡፡በአንዲት የመንደር ሃኪም ለሚሰጠው አገልግሎት 240 ብር መክፈሏን፤በመድሃኒትነት የማታውቀውን ፈሳሽ ነገር መጠጣቷንና ሃኪሙ ሆዷን ያሿት እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ከዚያ በኋላ የነቃችው ካረፈችባት የሩቅ ዘመድ የኪራይ ቤት ፍራሽ ላይ ነው፡፡ለአንድ ሳምንት ደም ይፈሳት የነበረችው ስምረት በወቅቱ ከፍተኛ ራስ ምታት አስቸግሯትም ነበር፡፡ከህመሙ አገግማ ቀና ማለት ስትጀምር ሌላ ሁኔታ ተፈጠረ፡፡"ከአልጋ ተነስቼ ቤት ማፅዳትና ምግብ ማብሰል ስጀምር ጓደኛዬ ከምትሰራበት ሆቴል አስቀጠረችኝ፡፡ህመሙ ቀስ በቀስ ቢለቀኝም ሰውነቴ ግን እየጨመረ መጣ፡፡በተለይ ሆዴ በየጊዜው ይገፋ ጀመር፡፡ስመረመር የአራት ወር እርጉዝ ሆኜ ተገኘሁ፡፡የዛን ቀን መሬት ተከፍታ ብትውጠኝ ደስታዬ ነበር፡፡ሃኪሞቹ ደግሞ ልንረዳሽ አንችልም አሉ፡፡እኔ ደግሞ ራሴን ለማጥፋት እያሰብኩ ነበር…"  ለያዥ ለገናዥ ያስቸገረችው የቀድሞ ተማሪ "…ያረገዝኩት ተገድጄ በመደፈሬ በመሆኑ…" ስትል ፈረመች፡፡እናም "አንድ ጊዜ ያረገዘችውን ሁለት ጊዜ አስወረደች"፡፡ስምረት ጥላቻና ህመም ተረፋት፡፡

No comments:

Post a Comment