Saturday, August 23, 2014

ደጉ ከሜሲና ከኔይማር ጋር ሊሠለፍ ነው

የኢትዮጽያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን (ዋልያ) የቀድሞው አምበል ደጉ ደበበ ኢትዮጵያን ወክሎ ከታዋቂዎቹ ሊዮኔል ሜሲ፣ ኔይማር ጋር በመጪው ነሐሴ 26 ቀን 2006 ዓ.ም. ሮም ኦሊምፒክ ስታዲየም በሚደረገው የወዳጅነት ጨዋታ ይሰለፋል፡፡

በዚህ ጨዋታም ዝነኛዎቹ የቀድሞ ተጫዋቾች ዲያጐ አርማንዶ ማራዶናና ዚነዲን ዚዳን ይሰለፋሉ፡፡

ይሄ ‹‹የሠላም ጨዋታ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ጨዋታ በካቶሊክ ፓፕ ፍራንሲስ ጀማሪነትና ቦነስ አይረስ ተቀማጭነቱን ያደረገውና በአርጀንቲናው ሃቪየር ዛኔቲ የተመሠረተው ፑፒ ፋውንዴሽን በሚባል ዕርዳታ ድርጅትና በፓንቲፊካል አካዴሚ ፎር ሶሻል ሳይንስ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የሕዝብ ግንኙነት አቶ ወንድሙ አላዩ ለሪፖርተር እንደገለጹት ከሆነ ይሄ ግብዣ የፊፋ አባል ለሆኑ አገሮች በሙሉ የተላከ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ፌዴሬሽንም ደጉ ደበበን መርጦታል፡፡ ደጉ ደበበ ለሁለት ዓመታት የዋልያ አምበል የነበረ ሲሆን፣ ኢትዮጵያን ከ31 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ እንድትሳተፍ ከፍተኛ ሚና ከተጫወቱ ተጫዋቾችም ውስጥ አንዱ ነው፡፡



ደጉ በዓለም ላይ ታዋቂ ከሚባሉት ከዋክብት ጋር በመሰለፉ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማው ለሪፖርተር የገለጸ ሲሆን፣ ፌዴሬሽኑም ይኼን ዕድል ለሱ በመስጠቱ ምሥጋናውን አቅርቧል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ደጉ ለወደፊቱ ተተኪዎች መጪው ጊዜ ብሩህ እንደሆነም ገልጿል፡፡ ‹‹የነገው ተተኪዎች ጠንክረው ከሠሩ ከዚህ የተሻለ ዕድል ያጋጥማቸዋል›› በማለት ደጉ ተናግሯል፡፡ ሠላምን በዓለም ለማስተዋወቅ ያተኮረው ይኼ ጨዋታ በተለይም ከጋዛ ሰርጥ በተነሳው ቀውስና እስከ 1,900 ለሚሆኑ ፍልስጥኤማውያን ህልፈትና 67 እስራኤላውያን ምክንያት ሆኗል፡፡

የፓፑን ግብዣ ተከትሎ የአርጀንቲና ተወላጆት የሆኑት ሊዮኔል ሜሲና ዲያጐ አርማንዶ ማራዶና በፍጥነት መልሰዋል፡፡ ፓፑም ‹‹በእስራኤልና በፍልስጥኤም መካከል ሠላም እንዲፈጠር ተጫወቱ›› የሚል መልዕክትም አስተላልፈዋል፡፡

ይኼ በተለያዩ እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚደረገው ጨዋታ ሮበርቶ ባጂዮ ፍራንሲስኮ ቶቲ፣ ቡፎን እንዲሁም የተለያዩ እምነት ተከታዮች ይሳተፉበታል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የእስራኤል ብሔራዊ ቡድን ኮከብ የሆነውና የቀድሞው የአርሴናልና የቼልሲ አማካኝ ዮሲ ቤናዩን መሳተፍ አንዳንድ ተጫዋቾችን አላስደሰተም፡፡

ብዙዎች ይሄንን ጨዋታ በጥሩ መልክ ቢቀበሉትም ታዋቂው ግብፃዊ ተጫዋች መሀመድ አቡትሪካ ይኼን ጨዋታ ውድቅ አድርጎታል፡፡ እስራኤል ባደረገችው ነገር ከፍተኛ ምሬት የተሰማው ይህ ተጫዋች ‹‹ከጋዛ ጋር እናዝናለን›› የሚል ጽሑፍ ያለበትም ቲ-ሸርት ለብሶ ታይቷል፡፡

መሀመድ አቡትሪካ በትዊተር ድረገጹ እንደገለጸው ‹‹ይኼ ፎቶ ፅዮናውያን የሚደግፍ በመሆኑ ምክንያት ያልተቀበልኩት ጨዋታ ነው፡፡ ይቅርታ እኛ አዲስ ትውልድ እያሳደግን ነው›› በሚል ገልጿል፡፡

በዚህ ጨዋታ ላይ የሚሰበሰበው ገንዘብ በፓፑ ገንዘብ ድጋፍ የሚያገኘውና በዓለም ላይ ጥራት ያለው ትምህርትን ለማስፈን ለሚሠራው ድርጅትና በቤተሰብና በልጆች መብት ላይ ለሚሠራው የፑፒ ፋውንዴሽን ገቢ ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ባለፈው ግንቦት ፖፑ የዛን ጊዜው የእስራኤልን ፕሬዚዳንት ሺሞን ፔሬዝና የፍልጥኤም ግዛት ፕሬዚዳንት መሀመድ አባስን በመጋበዝ ቫቲካን ላይ የፀሎት ፕሮግራም አዘጋጅተው ነበር፡፡
http://www.ethiopianreporter.com/

No comments:

Post a Comment