Monday, July 21, 2014

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለቢል ጌትስ የክብር ዶክትሬት ሊሰጥ ነው

ለማይክሮ ሶፍት መስራችና ባለቤት ለአሜሪካዊው ቢሊየነር ቢል ጌትስ በመጪው ሐሙስ  የክብር ዶክትሬት እንደሚሰጥ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ  አስታወቀ፡፡  ቢል ጌትስ የክብር ዶክትሬቱን ለመቀበል በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ዩኒቨርሲቲው ማረጋገጡን ለአዲስ አድማስ ገልጿል።
ቢል ጌትስ የማይክሮሶፍት ኩባንያን በማቋቋም ባገኙት ሃብት አፍሪካውያን ተማሪዎችን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ማድረጋቸውና በቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን አማካኝነት በኢትዮጵያ በተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ መሰማራታቸው ለክብር ዶክትሬቱ እንዳበቃቸው ተጠቁሟል፡፡
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባለፈው ቅዳሜ  8ሺህ ተማሪዎችን ያስመረቀ ሲሆን አትሌት ጥሩነሽ ዲባባን ጨምሮ ለ4 እውቅ ሰዎች የክብር ዶክትሬት ሰጥቷል። የቢል ጌትስ የክብር ዶክትሬት አሰጣጥ በተለየ ፕሮግራም እንዲካሄድ የተወሰነው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስምምነት የተዘጋጀ በመሆኑ ነው ያለው ዩኒቨርሲቲው፤ በመንግስት ደረጃ የክብር ዶክትሬት ሲሰጥ የአሁኑ የመጀመሪያው እንደሆነ ገልጿል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ በኔልሰን ማንዴላ አዳራሽ በመጪው ሃሙስ  በሚከናወነው የክብር ዶክትሬት አሰጣጥ ልዩ ስነ ስርአት ላይ ጥሪ የተደረገላቸው የውጭ አገር እንግዶች፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ምሁራን እንደሚገኙ ታውቋል፡፡

የዓለማችን እውቁ ባለሃብት ቢል ጌትስ ላለፉት 10 ዓመታት በሃብቱ መጠን ከዓለም አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ይዞ ላይ በመሆን የቆየ ሲሆን ዘንድሮም በ79.1 ቢሊዮን ዶላር ሃብት በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ፎርብስ መጽሔት የወጣው መረጃ ይጠቁማል። ቢል ጌትስ አሁን በግዙፍነቱ የሚታወቀውን ማይክሮሶፍት ለመመስረት ትምህርቱን አቋርጦ ከወጣበት ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ጨምሮ ከተለያዩ የአለማችን ታላላቅ ዩኒቨርሲቲዎች ስምንት ያህል የክብር ዶክትሬቶችን እንዳገኘ ለማወቅ ተችሏል፡፡
http://www.addisadmassnews.com

No comments:

Post a Comment