Friday, March 7, 2014

‹‹በገጠመኝ ችግር ምክንያት አዕምሮዬ በቀላሉ ያገግማል ብዬ አላስብም›› ወ/ሮ ዘነቡ ታደሰ፣ የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር


ባለፈው ሳምንት በትዊተር ገጻቸው የኡጋንዳ መንግሥት በቅርቡ በፀረ ግብረ ሰዶማዊነት ላይ ያወጣውን ጠንካራ ሕግ የሚፃረር መልዕክት የሰፈረባቸው የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር ወ/ሮ ዘነቡ ታደሰ፣ ሰሞኑን ከዋልታ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በጣም መጐዳታቸውን አስታወቁ፡፡ በቀላሉ አዕምሮአቸው እንደማያገግም ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሯ በትዊተር ገጻቸው ላይ የሠፈረው መልዕክት ከመጡበት ማኅበረሰብና ከዕምነታቸው አንፃር እሳቸውን ፈጽሞ የማይገልጽ መሆኑን አስታውቀው፣ የተፈጸመው ድርጊት ሰብዕናቸውን መንካቱን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከኑሮዬ፣ ከባህሌ፣ ከአስተዳደጌና ከሥራዬ አንፃር የሰፈረው መልዕክት አይገልጸኝም፤›› ብለዋል፡፡

ተጠለፈ በተባለው የትዊተር ገጽ ላይ የሠፈረው መልዕክት ፈጽሞ የእሳቸውንና የመንግሥትን አቋም እንደማይወክል አስረድተው፣ ‹‹ዘነብ በግል ብቻዋን አትታይም፡፡ እንደ መንግሥት ነው የምትታየው፡፡ አገርን ወክዬ ነው ያለሁት፡፡ የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶችን ጉዳይ ነው ይዤ ያለሁት፡፡ ሕገ መንግሥቱ ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ የወንጀለኞች መቅጫ ሕግ ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ስለዚህ እንደ መንግሥትም ሆነ በግል አቋማችን አይደለም፡፡ በመሆኑም ሰብዕናንና ሞራልን የሚፈታተን ነው፡፡ ሰብዕናዬ በእጅጉ ተነክቷል፡፡ በተፈጠረው ነገር ከልብ ነው ያዘንኩት፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ወ/ሮ ዘነቡ ግብረ ሰዶማዊነትን በተመለከተ ግልጽ አቋም እንዳላቸው ሲያብራሩ፣ እ.ኤ.አ. በ2013 በ57ኛው ‹‹ኮሚሽን ስታተስ ኦፍ ውሜን›› የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስብሰባ ላይ ተገኝተው የአፍሪካንና የአገራቸውን አቋም በግልጽ ማንፀባረቃቸውን አውስተዋል፡፡ አሁንም በዚህ ጉዳይ ላይ የፀና አቋም እንዳላቸው ገልጸው፣ ተጠለፈ በተባለው የትዊተር ገጻቸው ላይ የሠፈረው በጭራሽ የእሳቸውን አቋም የማያንፀባርቅ፣ ይልቁንም በእሳቸውና በቤተሰቦቻቸው ላይ ከፍተኛ ማኅበራዊ ጫና ያሳደረ አሳዛኝ ድርጊት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡


የትዊተር ገጽን የሚጠቀሙት በሴቶች፣ በሕፃናትና በወጣቶች ጉዳይ የተሠሩ ሥራዎችን ለማስተዋወቅ መሆኑን ጠቁመው፣ እሳቸው ፈጽሞ የእንዲህ ዓይነት ድርጊት ደጋፊም አራማጅም አለመሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶችን ጉዳዮች ከማስተዋወቅ ባሻገር በትዊተር ግንኙነት የማደርግባቸው ጉዳዮች የሉኝም፡፡ ከዚያ ውጪ የአገር ጉዳይ ሲነሳ መልስ እሰጥ ይሆናል፡፡ ከዚህ ቀደም በ2001 እና በ2008 የኢሜይል መጠለፍ ደርሶብኛል፡፡ ይኼ የመጀመርያ አይደለም፡፡ በኢሜይሌ ውስጥም ብዙም ሚስጥር የለም፡፡ ነገር ግን የአሁኑ በጣም የከፋና ሰብዕናን የሚነካ፣ የአገርን ገጽታ የሚያበላሽ በመሆኑና በሁለቱ አገሮች [ኢትዮጵያና ኡጋንዳ] መካከል የሚፈጥረውን አንድምታ ሳስበው ከባድ ነው፡፡ ቁስሉ ያማል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ቁስሉ በእኔ ብቻ አይደለም፤›› ያሉት ሚኒስትሯ፣ ወደ ቤተሰቦቻቸው መሸጋገሩን፣ ከዚያም አልፎ ተርፎ በማኅበረሰቡም ሆነ በሌላውም የሚፈጥረውን ጫና ማየት ይቻላል ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ከዚህ አንፃር ሳየው ከባድ ነው፡፡ እኔ ማለት የምችለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይፍረድ ነው፤›› በማለት የደረሰባቸውን ጫና አብራርተዋል፡፡ እሳቸው ከየካቲት 12 ቀን እስከ 16 ቀን 2006 ዓ.ም. ሰሜን ጐንደር፣ ከየካቲት 17 ቀን እስከ 20 ቀን 2006 ዓ.ም. ደግሞ ባህር ዳር ለሥራ ጉዳይ ሄደው እንደነበር ገልጸው፣ የትዊተር ገጻቸውን እንዳላዩት፣ ነገር ግን ሙሉ ቀን ስብሰባ ላይ ስለነበሩ ወሬው በሰፊው ተጋግሎ በስልክ ‹‹ምን ነክቶሻል?›› የሚሉ ሰዎች እንዳወሩላቸው፣ እሳቸው ደግሞ ግራ ተጋብተው እንደነበር ያስረዳሉ፡፡ በትዊተር ገጻቸው ላይ ተጽፏል ስለተባለው ጉዳይ ምንም የሚያውቁት ነገር ስላልነበረ ወሬው በሰፊው ተዛምቶ በተደጋጋሚ ሲደወልላቸው በአጭር መልዕክት ስለሚባለው ጉዳይ እንዲገለጽላቸው ጠይቀው ሲደርሳቸው፣ በሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት አማካይነት የእሳቸውም ሆነ የመንግሥት አቋም አለመሆኑን መግለጫ ለማውጣት መገደዳቸውን አስረድተዋል፡፡

ማኀበራዊ ጫናውን በተመለከተ ሲገልጹ፣ ‹‹ማኅበራዊ ጫናው አስከፊ ነበር፡፡ በልጆቼ ላይ ያደረሰውን ጫና ይኼ ነው ልል አልችልም፡፡ ቃላት ያጥሩኛል፡፡ ይኼ ችግር በቤተሰቤ ላይ ቀላል አልነበረም፡፡ እንግዲህ ችግሩ ሲፈጠር ቤተሰቦቼ ከጐንደር ነው የመጡት፡፡ ዘነብ ምን ሆነች? በጤናዋ ነው? አለች ወይ? እስከዚህ ድረስ ጫናው ከባድና ሰብዕና የሚነካ ነበር፡፡ ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ላይ ተቀምጬ ነገር ይብሰለሰላል ወይስ ሥራ ይሠራል? ወይስ ወዴት ነው የማመራው?›› ብለዋል፡፡

የትዊተር ገጻቸው በመዘጋቱ ምክንያት እስከ መቼ ተዘግቶ እንደሚቆይና ካሁን በኋላስ ይቀጥሉበታል ወይ? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ለመወሰን በጣም ከባድ እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹በገጠመኝ ችግር ምክንያት አዕምሮዬ በቀላሉ ያገግማል ብዬ አላስብም፤›› ያሉት ወ/ሮ ዘነቡ፣ ከእሳቸው አልፎ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ልጆቻቸው ትምህርታቸውን መከታተል አለመቻላቸውን አስረድተዋል፡፡

‹‹ልጆቼ ‹እቴትዬ የተፈጠረው ነገር ምንድነው?› ነው ያሉት፡፡ ስለዚህ ዘነብ ተረጋግታ ወደዚህ ትገባለች? አዕምሮዬን ማረጋጋት እፈልጋለሁ፡፡ ከየቦታው የሚደወለው ስልክ ከባድ ነው፡፡ የሚመጣው መልዕክት ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ አዕምሮዬን አረጋግቼ ወደሚቀጥለው እንዴት እገባለሁ? የሚለውን በተረጋጋ አኳኋን መልስ ብሰጥ ይሻለኛል፡፡ ለጊዜው ግን ዝምታ ነው የምመርጠው፤›› ብለዋል፡፡    
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment