Monday, March 24, 2014

ከሰው ለሰው ድራማ የሚገኘው ገቢ ለማንም እንዳይከፈል በፍርድ ቤት እግድ ተጣለበት



በየሳምንቱ ረቡዕ ማታና በድጋሚ ቅዳሜ ላለፉት 127 ሳምንታት በመተላለፍ ላይ ካለው ‹‹ሰው ለሰው›› ድራማ የሚገኘው ማንኛውም ዓይነት ገቢ ለማንም እንደይከፈል፣ መጋቢት 2 ቀን 2006 ዓ.ም. በፍርድ ቤት ዕግድ ተጣለበት፡፡

ክፍያው እንዳይፈጸም በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የግልግል ዳኞች ክልከላ የተጣለባቸው፣ አቶ መስፍን ጌታቸው (በአሁኑ ጊዜ የድራማው ፕሮዲዩሰርና ዳይሬክተር) አቶ ሰለሞን ዓለሙ (ስክሪፕት ጸሐፊ ተዋናይ)፣ አቶ ነብዩ ተካልኝ (የኢትዮ ኢንተር ኤጁኬት ፕሮሞሽን ባለቤት)፣ የአቶ ዳንኤል ኃይሌና የአቶ ሰለሞን ዓለሙ ስፓርክ ፊልም ፕሮዳክሽን የሚባለው ድርጅት ናቸው፡፡

የግልግል ዳኞቹ የዕግድ ትዕዛዙን ያስተላለፉበት ምክንያት፣ የሰው ለሰው ድራማ ፕሮዲዩሰርና በድራማው ‹‹ናርዶስ›› የምትባለውን ገጸ ባህሪ ወክላ የምትተውንና በፋይናንስና አድሚኒስትሬሽን ኃላፊነት ትሠራ ከነበረችው ወ/ሮ ብሥራት ገመቹ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ክስ በመመሥረቱ መሆኑን የዕግድ ትዕዛዙ ያስረዳል፡፡

ወ/ሮ ብሥራት ገመቹ፣ አቶ ነብዩ ተካልኝ፣ አቶ መስፍን ጌታቸው፣ አቶ ሰለሞን ዓለሙና አቶ ዳንኤል ኃይሌ ታኅሣሥ 22 ቀን 2003 ዓ.ም. በሰነዶችና ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ለማዘጋጀት ተስማምተው የሽርክና ውል መፈራረማቸውን የክስ ማመልከቻው ያስረዳል፡፡


ቀድሞ ‹‹የመጨረሻው ሰሞን›› የሚል ስያሜ ሰጥተውት የነበረውን ድራማ ‹‹ሰው ለሰው›› በማለት ሰይመው ለመሥራት ሲስማሙ፣ ወ/ሮ ብሥራትና ሦስቱ ተከሳሾች የትርፍ ክፍፍላቸውን በመቶኛ እንደየተሳትፏቸው ለመከፋፈል ተስማምተው መፈራረማቸው በሰነዶቹ ላይ ተጠቅሷል፡፡

ኢትዮ ኢንተር ኤጁኬት ፕሮሞሽን በተባለው የአቶ ነብዩ ተካልኝ የንግድ ድርጅት ፈቃድ፣ ከኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጋር ውል ተፈራርመው ‹‹ሰው ለሰው›› ድራማን በመሥራት ላይ እያሉ፣ ንግድ ፈቃዳቸውን ሲያድሱ የአቶ ሰለሞን ዓለሙ ድርጅት መሆኑ በተጠቀሰው ስፓርክ ፊልም ፕሮዳክሽን በሚል ድርጅት ስም በማደስ፣ ከሳሽ ወ/ሮ ብሥራት የትርፍ ተካፋይ የማትሆንበት አሠራር መጀመሩን ክሱ ይገልጻል፡፡  22 ማዞሪያ አካባቢ በሚገኘው ቡና ባንክ ቅርንጫፍ አቶ ሰለሞን ዓለሙና አቶ መስፍን ጌታቸው በጋራ ሒሳብ ሲያንቀሳቅሱ እንደነበርም የክሱ አቤቱታ ይጠቁማል፡፡

ለድራማው ቀረፃ ቤቷንና መኪናዋን በማቅረብ ተባብራ ስትሠራ የነበረችው ከሳሽ ወ/ሮ ብሥራት ድራማው ከተጀመረ ጀምሮ በፕሮዲዩሰርነት፣ በፋይናንስ አድሚኒስትሬሽን በወር አምስት ሺሕ ብር ተከፍሏትና ‹‹ናርዶስ›› የተባለችውን ገጸ ባሕሪ ወክላ ትሠራ እንደነበርም ለፍርድ ቤት ያቀረበችው ሰነድ ያብራራል፡፡

በመሆኑም በኃላፊነትም ሆነ በተዋናይነት እንዲሁም ከትርፍ ሊከፈላት የሚገባው ክፍያ ሳይፈጸምላት፣ ለጊዜው በግልጽ መግለጽ በማትፈልገው ምክንያት ከአንዱ ተከሳሽ ጋር አለመግባባት በመፈጠሩ፣ ከድራማው 54ኛ ክፍል ጀምሮ ‹‹ናርዶስ››ን ሆና ትተውንበት የነበረውን ገጸ ባህሪ መነጠቋን፣ ከ90ኛው ክፍል ጀምሮ ደግሞ ከፕሮዲዩሰርነቷ መሰረዟን በክሷ ለፍርድ ቤቱ አስረድታለች፡፡ ከድራማው 26ኛ ክፍል ጀምሮም የገቢ ክፍፍል እንዳልተፈጸመላት አክላለች፡፡

አቶ መስፍንና አቶ ሰለሞን ከተለያዩ ስፖንሰሮችና ከኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት መጠኑን ያላወቀችው ክፍያ እያሰባሰቡ ለግል ጥቅማቸው እያዋሉት መሆኑን፣ አቶ ዳንኤል የተባሉት ተከሳሽም የጥቅም ተጋሪ መሆናቸውን አስረድታ፣ 100 ሺሕ ብር በካሽ አዋጥታ ካቋቋመችው የድራማ መድረክ በዕውቀትና በዓይነት ከሰጠችው አገልግሎት በላይ ሞራል የሚነካ (ለኢትዮጵያ ሕዝብ ክብር ሲባል የማይገለጽ) ተግባር እንደተፈጸመባት በክሷ ዘርዝራ አቅርባለች፡፡

ከሳሽ ወ/ሮ ብሥራት ከቴሌቪዥን፣ ከማስታወቂያና ከስፖንሰሮች ከተሰበሰበውና የአገር ውስጥ ገቢ ተቀንሶ የሚደርሳት 16.25 በመቶ ድርሻዋ በወራት ተባዝቶ ከነወለዱ እንዲከፈላት፣ በፋይናንስና አድሚኒስትሬሽን ለሠራችበት በወር የሚከፈላትን አምስት ሺሕ ብር በ35 ወራት ተባዝቶ እንዲከፈላት፣ ‹‹ናርዶስ›› የምትባለውን ገጸ ባህሪ ወክላ ለተወነችበት 56 ክፍሎች በ500 ብር ታስቦ በድምሩ 163 ሺሕ ብር እንዲከፈላት ዳኝነት ጠይቃለች፡፡

የከሳሽን አቤቱታ ዝርዝር ማብራሪያ የተመለከተው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ንፋስ ስልክ ላፍቶ ምድብ ሁለተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት በሰጠው ብይን፣ ከሳሽና ተጠሪዎች እያንዳንዳቸው አንድ ዳኛ እንዲመርጡ፣ የግራ ቀኙን ተከራካሪ የሚሰበስብ ዳኛ በጋራ እንዲመርጡና በሽምግልና ዳኝነት እንዲታይ የተወሰነ ቢሆንም፣ በአንድ ወር ውስጥ መምረጥ ባለመቻላቸው በፍርድ ቤቱ ሬጅስትራር በኩል የግልግል ዳኛ እንዲሾም አዞ ነበር፡፡

የግልግል ዳኞች በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን አቤቱታ በመመርመር ላይ ቢሆኑም፣ ከሳሽ ወ/ሮ ብሥራት የግልግል ዳኝነቱ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ከድራማው የሚገኘው ገቢ እንዲታገድላት ለግልግል ዳኞቹ ማመልከቻ በማቅረብዋ፣ የግልግል ዳኞቹ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 154 መሠረት ክርክሩ እልባት እስከሚያገኝ፣ ለተጠቀሱት ተከሳሾችም ሆነ ለሦስተኛ ወገን ምንም ዓይነት ክፍያ እንዳይፈጸም የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥንን ድርጅት ታዟል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment