Thursday, March 27, 2014

‹‹ኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት የሰፈነባትና ሰዎች በነፃነት ሐሳባቸውን የሚገልጹባት እንድትሆን ምኞቴ ነው››



ዶ/ር ፍራንክ ዋልተር ስተይንመር፣ የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ፍራንክ ዋልተር ስተይንመር የአንድ ቀን የኢትዮጵያ ጉብኝት፣ በመንግሥት ባለሥልጣናትና በመንግሥት ሚዲያዎች ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ነበር፡፡

ዶ/ር ስተይንመር ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ከፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ጋር ተገናኝተው በሁለትዮሽ ግንኙነትና በአካባቢያዊ የደኅንነት ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መምከራቸው፣ ጀርመን ለኢትዮጵያ ያላት ግምት ከፍተኛ መሆኑን አመላካች ነው፡፡

በአፍሪካ በሦስት አገሮች ወሳኝ የተባለለትን ጉብኝታቸውን በኢትዮጵያ የጀመሩት ዶ/ር ስተይንመር፣ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር የምታደርገው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትብብር ከሁለትዮሽ ግንኙነት በላይ መሆኑ አመላካች እንደሆነ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡

በጀርመን ከመራሄ መንግሥት አንገላ መርከል ቀጥለው ወሳኝ እንደሆኑ ተደርገው የሚታዩት ዶ/ር ስተይንመር፣ አንድ ትልቅ የባለሀብቶች ቡድን መርተው የመጡ ሲሆን፣ መንግሥታቸው በኢትዮጵያ ያየው ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ኢንቨስትመንት እንዲያፈስ አነሳስቶታል፡፡



የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከአቻቸው ከዶ/ር ቴድሮስ ጋር ከመከሩ በኋላ ማክሰኞ ረፋዱ ላይ ለጋዜጠኞች በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አኅጉር በራሷ የምትቆምና በራሷ የምትተማመን አገር ሆና ማየት እንደሚፈልጉ ገልጸው፣ ‹‹የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት የሰፈነባት፣ የሲቪክ ማኅበረሰቦች በነፃ የሚንቀሳቀሱባትና ሰዎች በነፃነት ሐሳባቸውን የሚገልጹባት አገር ሆና ማየት እፈልጋለሁ፤›› ሲሉ ምኞታቸውን ተናግረዋል፡፡

በርከት ያሉ የአገራቸውን ኢንቨስተሮችና የመንግሥት ኃላፊዎች ይዘው ለመምጣት ያነሳሳቸው፣ ኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት ባስመዘገበችው የኢኮኖሚ ዕድገት ምክንያት መሆኑንም ደጋግመው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ለሌሎች አፍሪካ አገሮች ምሳሌ መሆኑና በአገሪቱ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት አማራጭ መኖሩ የአገራቸውን ትላልቅ ኩባንያዎች ቀልብ የሳበ እንደሆነ ከንግግራቸው መረዳት ተችሏል፡፡

የጀርመን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ባለው ነፃ ገበያ ግንባር ቀደም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይፈልጋሉ፡፡ በአሁኑ ጉብኝት ባለሀብቶች የሚበዙበት ከፍተኛ የልዑካን ቡድን መርተው ቀድመው ወደ ኢትየጵያ ለመምጣታቸው ሚስጥሩም ይኼው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በራሷ የምትቆመውና የራስ መተማመኗም የሚፈጠረው በዚህ ሁኔታ እንደሆነም አክለዋል፡፡ የሁለቱም አገሮች የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ ለማድረግ የመንግሥታቸው ዕቅድ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

‹‹አመሰግናለሁ›› የሚል ትርጉም ያለው ‹‹ዳንክሽን›› በሚል የጀርመንኛ ቃል ንግግራቸው በመጀመር ጋዜጠኞችንና የልዑካን ቡድኑን አባላት ፈገግ ያሰኙት ዶ/ር ቴድሮስ በበኩላቸው፣ በቅርቡ በተጠናቀቀው የአውሮፓውያን ዓመት የጀርመን መራሄ መንግሥት አንገላ መርከል፣ ቀጥሎም በተከታታይ የአገሪቱ የግብርና ሚኒስትርና የአገሪቱ የኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ጉብኝት ተከትሎ የአሁኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉብኝት መሆኑን አስረድተው፣ ይህንን ጉብኝት የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ትርጉም እንደሚሰጠው ተናግረዋል፡፡ ‹‹በአምስትና በስድስት ወራት ውስጥ ከፍተኛ የጀርመን መንግሥት ባለሥልጣናትን ጉብኝት እያስተናገድን ነው፡፡ ይኼ ራሱን የቻለ ትርጉም አለው፡፡ የግንኙነታችን ደረጃ በራሱ ይናገራል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹አሁን በመካከላችን የሚገኙት ዶ/ር ስተይንመር ደግሞ፣ በበለጠ ትልቅ የባለሀብቶች ልዑካን ቡድን መርተው ነው የመጡት፤›› ያሉት ዶ/ር ቴድሮስ፣ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠነከረ ለመሆኑ ማሳያ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ንግድና ኢንቨስትመንት የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ዲፕሎማሲ ዋነኛ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፣ ጀርመን ከአውሮፓ ትልቋ የንግድ ልውውጥ አገር መሆኗንም አክለዋል፡፡

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር 15 ዲፕሎማቶችን ለማሠልጠን ቃል ስለተገባላቸው ያመሰገኑት ዶ/ር ቴድሮስ፣ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ዕድል አግኝተው በጀርመን ሥልጠናቸውን አጠናቀው የተመለሱት ቁጥራቸው በርከት ያሉ ኢትዮጵያዊያን ጠቃሚ የሆነ ዕውቀት አካብተው መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም በጥናትና ምርምር ዙርያ የአቅም ግንባታ ድጋፍ ለማድረግ ከጀርመን አቻቸው ቃል እንደተገባላቸው ገልጸው፣ ይህም ሁለቱም መሥሪያ ቤቶች ተቀራርበው እንዲሠሩ በትልቁ በር የሚከፍት እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡

‹‹ከሁለትዮሽ በላይ ወዳጅነት››

በአውሮፓ ትልቁን ኢኮኖሚ የምታንቀሳቅሰው ጀርመን የአውሮፓ ኅብረት ሞተር ተደርጋ ትወሰዳለች፡፡ ቀደም ሲል የአውሮፓ አገሮችን ኢኮኖሚ ያናጋው የገንዘብ ቀውስ እምብዛም ተፅዕኖ ያላሳደረባት አገር ነች፡፡ እንዲያውም የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች ከዚህ ቀውስ እንዲወጡ ከፍተኛውን ሚና እንደተጫወተች በስፋት ይነገራል፡፡ ኢትዮጵያ በበኩሏ በአፍሪካ ኅብረት ውስጥ ያላት የፖለቲካ ተፅዕኖ፣ እንዲሁም በምሥራቅ አፍሪካ የሚከሰቱ ግጭቶችን ለመፍታት የምታደርው ጥረት የሁለቱም ሚኒስትሮች ንግግሮች ዋነኛ ማጠንጠኛ ነበሩ፡፡

ዶ/ር ስተይንመር እንደሚሉት፣ ‹‹ጀርመን በአውሮፓ ባሉ ወሳኝ ጉዳዮች ግንባር ቀደም ሆና ትንቀሳቀሳለች፡፡ ኢትዮጵያም የአፍሪካ ኅብረትና የሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ ነች፤›› ብለው፣ ሁለቱም አገሮች የሚያደርጉት የፖለቲካ ትብብር የአኅጉር ከአኅጉር ያህል ትርጉም ያለው ነው ብለዋል፡፡

ዶ/ር ቴድሮስ የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ካብራሩ በኋላ ወንድማዊ ወዳጅነት በተሞላው ፈገግታ የጀርመኑ አቻቸውን እየተመለከቱ፣ ‹‹የሚገርማችሁ የቅርብ ጓደኛዬ ናቸው፡፡ እናም ለደቡብ ሱዳንና ለሶማሊያ ጉዳዮች እጅግ ተቆርቋሪ ናቸው፡፡ በየጊዜው እየደወሉ ይጠይቁኛል፡፡ በግላቸው የሚያደርጉት ጥረት በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ላመሰግናቸው እወዳለሁ፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በየአካባቢያችን ያሉትን ችግሮች ለመፍታት የምንንቀሳቀስ ነን፤›› በማለት ጀርመን ለደቡብ ሱዳን ቀውስ መፍትሔ ለመፈለግ ኢትዮጵያ የምታደርገውን ጥረት እንደምትደግፍ የተናገሩት ዶ/ር ስተይንመር፣ አገራቸው በማናቸውም አካባቢያዊ የፀጥታ ጉዳዮች ለመተባበር ዝግጁ ናት ብለዋል፡፡ በደቡብ ሱዳን ለተፈጠረው ቀውስ አስፈላጊውን ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማድረግ ጀርመን ቃል የገባች መሆኗንና በሶማሊያም ተመሳሳይ ዕቅድ እንዳላት አስረድተዋል፡፡

በአፍሪካ ለሚታዩት ቀውሶች የአፍሪካ አገሮች ራሳቸው ሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲያሰማሩ ፍላጎት ያላት ጀርመን፣ አስፈላጊውን የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግ ሁሌም ዝግጁ መሆኗን ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት አረጋግጠውላቸዋል፡፡

‹‹ትብብር በሁለት አገሮች መካከል ተብሎ የሚተላለፍ ሳይሆን፣ ከዚያም ባለፈ ሁለቱም አገሮች በየአካባቢያቸው የሚጫወቱት ተመሳሳይ ሚና መገለጫ ነው፤›› ሲሉ ዶ/ር ቴድሮስ በማጠቃለያ ንግግራቸው አስታውቀዋል፡፡

የጀርመንና የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ሲሆን፣ ለኢትዮጵያ ቡና ከአውሮፓ ቀዳሚ የገበያ አገር መሆኗን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment