Monday, March 10, 2014

መንግሥት ለቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ መኖርያ ቤት ሊገነባ ነው


መንግሥት ለተሰናባቹ ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ መኖርያ ቤት እንዲገነባላቸው ውሳኔ አሳለፈ፡፡ የቀድሞውን ፕሬዚዳንት መኖርያ ቤት የመገንባቱን ኃላፊነት የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ተረክቧል፡፡

የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ የቀድሞውን ፕሬዚዳንት መኖርያ ቤት በንፋሰ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ሦስት ቁጥር ማዞሪያ አካባቢ ለመገንባት መዘጋጀቱን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ኤጀንሲው የራሱ ይዞታ የሆነ ቪላ ቤት አፍርሶ ለአቶ ግርማ እንደሚመች አድርጎ ለመገንባት ዲዛይኑን ለማሠራት ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡ የመኖርያ ቤቱን ግንባታም ለግል ሥራ ተቋራጭ እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡

በአምስት ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያርፋል ተብሎ የሚጠበቀው የአቶ ግርማ የወደፊት መኖርያ ቤት፣ ሁሉንም ዓይነት አገልግሎቶች መስጫ እንዲኖረው ተደርጎ ይገነባል ሲሉ ምንጮች ገልጸዋል፡፡


ላለፉት 12 ዓመታት የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር የነበሩት አቶ ግርማ ባለፈው መስከረም መንበራቸውን ለዶ/ር ሙላቱ ተሾመ አስረክበዋል፡፡ አቶ ግርማ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የነበሩ በመሆናቸው ከብሔራዊ ቤተ መንግሥት ሲወጡ ወደ ቀድሞ መኖርያ ቤታቸው አልተመለሱም፡፡ በወቅቱ በመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ሥር የሚመጥናቸው መኖርያ ቤት ባለመገኘቱ መንግሥት ውድ በሚባል ዋጋ የመኖርያ ቤት ተከራይቶላቸዋል፡፡

የአቶ ግርማ የአሁኑ የኪራይ መኖርያ ቤት የሚገኝው በየካ ክፍለ ከተማ በተለምዶ 22 ማዞርያ አካባቢ ከአክሱም ሆቴል ጀርባ ነው፡፡ መኖርያ ቤቱ ባለ ሁለት ፎቅ ሲሆን፣ የመዋኛ ገንዳን ጨምሮ የተለየዩ አገልግሎት መስጫዎችን አካቷል፡፡

መንግሥት ለዚህ መኖርያ ቤት ኪራይ በየወሩ አራት መቶ ሺሕ ብር ወጪ ያወጣል የገንዘቡ መጠን ከፍተኛ ነው በሚል ምክንያትና መንግሥት ለተሰናባች ፕሬዚዳንት ስለሚያቀርባቸው ጥቅማ ጥቅሞች ተደንግጎ እያለ እንዴት ቀደም ብሎ መዘጋጀት አልተቻለም የሚሉ ጥያቄዎች በሰፊው ሲነሱ ቆይተዋል፡፡ ምክንያቱም ከአሥር አመት በፊት የወጣው አዋጅ ቁጥር 255 ተሰናባች ፕሬዚዳንት ስለሚያገኛቸው ጥቅማ ጥቅሞች፣ እንዲሁም ደረጃውን የጠበቀ መኖርያ ቤት እንደሚሰጥ ይደነግጋል፡፡

ነገር ግን አቶ ግርማ ከብሔራዊ ቤተ መንግሥትን በሚለቁበት ወቅት የፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት መኖርያ ቤት ለመከራየት ተገዷል፡፡

አሁን ግን መንግሥት ኃላፊነቱን ለመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ በመስጠት ለቀድሞው ፕሬዚዳንት መኖርያ ቤት ለመገንባት ዝግጅት ጀምሯል፡፡
http://ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment