Monday, March 3, 2014

የአዲስ አበባ ወጣቶች ፎረም ፀረ ግብረ ሰዶማዊነት ሰላማዊ ሠልፍ ለማካሄድ ጥያቄ አቀረበ



ከ55 ሺሕ በላይ አባላት አሉኝ የሚለው የአዲስ አበባ አስተዳደር ወጣቶች ፎረም፣ ሁለት መቶ ሺሕ ሰዎች ተሳታፊ የሚሆኑበት ፀረ ግብረ ሰዶማዊነት ሰላማዊ ሠልፍ በመጋት ወር 2006 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ለማካሄድ ጥያቄ አቀረበ፡፡

ከቀናት በፊት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደብዳቤ ማስገባቱን፣ የፎረሙ ወጣት ተኮር ዘርፍ ሰብሳቢ ኃይለ ሚካኤል ብዙአየሁ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

ፎረሙ ሰላማዊ ሠልፍ ብቻም ሳይሆን የሃይማኖት ተቋማትን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት ተወካዮች የሚገኙበትና ብዙዎች የሚካፈሉበት የውይይት መድረክ ለማድረግ ማቀዱም ተገልጿል፡፡ ፎረሙ የፀረ ግብረ ሰዶማዊነት ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ ለከተማ አስተዳደሩ ጥያቄ ያቀረበው፣ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የግብረ ሰዶማውያንን ሕይወት የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም ካሳተመው ወይንዬ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከሚሰኝ መንፈሳዊ ማኅበር ጋር በመተግበር እንደሆነ ኃይለ ሚካኤል ተናግሯል፡፡


ሰላማዊ ሠልፍ ለመጥራት መነሻ የሆነው ግብረ ሰዶማዊነት አስጊ ደረጃ ላይ እየደረሰ በመሆኑ፣ ኅብረተሰቡንና መንግሥትንም ስለችግሩ ለማስገንዘብ መሆኑን ሁለቱ ጥያቄ አቅራቢዎቹ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ግብረ ሰዶማውያን ይደብደቡ፣ ይታሰሩ ሳይሆን ካሉበት ሕይወት እንዲወጡ ይደረግ፡፡ ሌሎች እንዳይገቡም ሥራዎች ይሠሩ ለማለት ነው፤›› ብሏል ኃይለ ሚካኤል፡፡  

በሌላ በኩል ባለፈው ዓመት ሰኔ 23 ቀን 2005 ዓ.ም. በርካቶች በተገኙበት በቸርችል ሆቴል ‹‹ስለኢትዮጵያ ዝም አንልም ግብረ ሰዶማዊነት በኢትዮጵያ የ666 አሠራር›› በሚል በተዘጋጀ መድረክ ላይ በተመረቀው ዘጋቢ ፊልም ላይ የተሳተፉ ግብረ ሰዶማውያን (አሁን ከዚያ ሕይወት ወጥተናል ብለዋል) ማንነታቸው በመታወቁ፣ በተለያዩ መንገዶች ጥቃት እየደረሰባቸው መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በፊልሙ ላይ የተሳተፉት ግለሰቦች እንደሚሉት፣ የፊልሙ ዋና አዘጋጅና የማኅበረ ወይንዬ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሊቀመንበር መምህር ደረጀ ነጋሽ ማንነታቸው እንዳይለይ ምሥላቸውን በአግባቡ ባለመሸፈናቸውና ድምፃቸውንም በተወሰነ ደረጃ ባለመቀየራቸው፣ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ችግር ውስጥ ወድቀዋል፡፡

በግብረ ሰዶማዊነት ሕይወት ውስጥ እያሉ ጓደኞቻቸው በነበሩና አሁንም ግብረ ሰዶም በሆኑ ጓደኞቻቸው ለምን ስለሕይወታችን አደባባይ ወጥታችሁ ምስክርነት ሰጣችሁ በሚል ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የሚገባው ጥንቃቄ ባለመወሰዱ በሚኖሩበት አካባቢ የሚያውቋቸው ሰዎች በቀላሉ ስለለዩዋቸው በተለያዩ መንገዶች ጥቃት እየደረሰባቸው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በዘጋቢ ፊልሙ ምስክርነቷን የሰጠች አንዲት ሴት፣ ‹‹የሠፈሬ ሰዎች እኔ መሆኔን በማወቃቸው ችግር ውስጥ ወድቄአለሁ፡፡ ከቦታ ቦታ ቤት እየቀያየርኩ ለመከራየት ተገድጃለሁ፤›› ስትል ለሪፖርተር ተናግራለች፡፡ በተመሳሳይ በዘጋቢ ፊልሙ ላይ የተሳተፈ ወጣት ከግብረ ሰዶም ሕይወት ወጥቶ በየመንገዱ የክብደት ሚዛን መሥራትን ቢመርጥም፣ በሽያጭ የተሠራጨውን ዘጋቢ ፊልም የተመለከቱና የለዩት ሰዎች እንዳይሠራ እያደረጉት እንደሆነ አስረድቷል፡፡ ዘጋቢ ፊልሙ ላይ የተሳተፈ ሌላ ጓደኛቸው በፊልሙ ምክንያት ከሰዎች ጋር ተጣልቶ በአሁኑ ወቅት ማረሚያ ቤት እንደሚገኝ ገልጿል፡፡

እነዚህ ሰዎች ትልቅ ችግር ደረሰብን የሚሉት በመጀመርያ ደረጃ በፊልሙ ላይ ማንነታቸው እንዳይለይ ጥንቃቄ ባለመደረጉ ይሁን እንጂ፣ በፊልሙ አዘጋጅ ላይ ሌሎች ቅሬታዎችንም ያነሳሉ፡፡ አዘጋጁ፣ ‹‹በቀጣይ ኑሯችሁን የምትደጉሙበትን ሁኔታ አመቻቻለሁ፤›› ቢልም፣ በገባላቸው ቃል መሠረት ምንም እንዳላደረገላቸው ተናግረዋል፡፡

ጉዳዩን በሚመለከት ጥያቄ የቀረበላቸው መምህር ደረጀ በፊልሙ ዝግጅት ላይ የምስክርነት ሰጪዎችን ገጽ ለመከለል ሲሞክሩ ድምፃቸው መቀየሩን፣ ነገር ግን ተዓማኒነትን ይቀንሳል በሚል እንደተተወና ምስክርነት የሰጡ ሰዎችም በዚህ ተስማምተው እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ግለሰቦቹ በቅርቡ በተለየ ሶፍትዌር በመጠቀም የተከለለው ገጽታቸው በግልጽ እንዲታይ ተደርጐ በኢንተርኔት መለቀቁ ችግራቸውን የበለጠ እንዳበረታው ሲናገሩ፣ መምህር ደረጀም የግለሰቦቹ ገጽ የሚታይበት ፊልም በቅርቡ ማንነቱ ባልታወቀ አካል በፌስቡክ መለቀቁን አስታውቀዋል፡፡ እሳቸው እንደሚጠረጥሩት፣ ይህን ያደረጉት ግብረ ሰዶም በኢትዮጵያ እንዲስፋፋ የሚፈልጉና ዘጋቢ ፊልሙ ለሕዝብ በመውጣቱ የተበሳጩ ናቸው፡፡

እሳቸው እንደሚሉት ለፊልሙ ሦስት መቶ ሺሕ ብር ወጪ ሆኗል፡፡ ፊልሙ ለሕዝብ አስተማሪ ይሆን ዘንድ በነፃ እንዲታደል ታስቦ የነበረ ቢሆንም፣ እንደታሰበው ስፖንሰር ባለመገኘቱ ተሽጧል፡፡ በአጠቃላይ የታተመው አሥራ አምስት ሺሕ ሲዲ ሲሆን፣ የተሸጠው በሃያ አምስት ብር ሒሳብ አሥራ ሁለት ሺሕ ሲዲ ብቻ መሆኑን መምህር ደረጀ ይናገራሉ፡፡

በፊልሙ ላይ ምስክርነት የሰጡት ግለሰቦች አንዳንዶቹ አስተማሪ ይሆን ዘንድ በነፃ መሳተፋቸውን በፊርማ ያረጋገጡ ሲሆን፣ ያልፈረሙ መኖራቸውን የሚናገሩት መምህር ደረጀ፣ ስፖንሰር ይገኛል በሚል ለግለሰቦቹ ቃል ገቡ እንጂ ክፍያን ወይም ጥቅማ ጥቅምን በሚመለከት የተፈራረሙት ነገር አለመኖሩን ያስረዳሉ፡፡

‹‹ሕዝብን ለማስተማር ሲሉ ራሳቸውን ያወጡ በመሆናቸው ሰዎች ማንነታቸውን መለየት ቢችሉ እንኳ ሊያጠቋቸው ይችላሉ የሚል ጥርጣሬ አልነበረኝም፡፡ ሕዝቡ አሁንም እነዚህን ሰዎች መደገፍ አለበት፤›› ብለዋል መምህር ደረጀ፡፡          
http://www.ethiopianreporter.com 

No comments:

Post a Comment