Thursday, February 13, 2014

‹‹የተቃዋሚ ድርጅት አባል ሆኖ ከመንግሥት ሥራ ማግኘት ከባድ ነው››


ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ የኮንስትራክሽን ሥራና የሆቴል ባለቤት
ተወልደው ያደጉት በኦሮሚያ ክልል ጂማ ዞን ሊሙ ኮሳ ወረዳ ጋሉ አካባቢ ነው፡፡ ትምህርታቸውን በጂማ ዞን ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ከተከታተሉ በኋላ በመምህርነት አገልግለዋል፡፡

ለዓመታት በጂማ ማዘጋጃ ቤት ከዚያም ባቱ (ዝዋይ) ከተማ በሚገኘው ሼሪ ኢትዮጵያ አበባ እርሻ ውስጥ በቴክኒካል ማኔጀርነት ሠርተዋል፡፡ ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ በአሁኑ ወቅት የራሳቸውን የኮንስትራክሽን ኩባንያ አቋቁመውና በመቂ ከተማ  ሆቴል ከፍተው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ኢንጂነር ዘለቀ ከቢዝነስ ሥራቸው ውጭ በፖለቲካም ንቁ ተሳታሳፊ ናቸው፡፡ ሥራቸውን አስመልክቶ ውድነህ ዘነበ አነጋግሯቸዋል፡፡



ሪፖርተር:-  በሆቴልና በኮንስትራክሽን ሥራዎች ውስጥ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ሥራዎች ውስጥ ሆቴሉ በምን ደረጃ እንደሚገኝ ቢገልጹልኝ?

ኢንጂነር ዘለቀ:- ሆቴሉ የሚገኘው ከአዲስ አበባ ወደ ሐዋሳ በሚወስድ መንገድ ላይ በምትገኘው መቂ ከተማ ነው፡፡ የቱሪስት ማረፊያ የቱሪስት መሸጋገሪያ ለማድረግ ሆቴሉን በአዲስ መልክ  እንደገና ልገነባ እየተዘጋጀሁ ነው፡፡

ሪፖርተር:- በኮከብ ደረጃ ለማሳደግ ነው?

ኢንጂነር ዘለቀ:- አዎ፡፡ በኮከብ ደረጃ ለማሳደግ ነው እቅዴ፡፡ ምክንያቱም መስመሩ የቱሪስት ነው፡፡ በርካታ ቱሪስቶች ይመጣሉ፡፡ ሆኖም በመስመሩ ጥሩ ሆቴል አያገኙም፡፡ የግድ ሐዋሳ መጓዝ ይኖርባቸዋል፡፡ አማካይ ቦታ ላይ ጥሩ ሆቴል ቢሠራ ከሚል ነው ይህንን እቅድ ያመነጨሁት፡፡ አሁን ነባሩን ሆቴል አፍርሼ ዘመናዊ ባለ ኮከብ ሆቴል ለመገንባት ዲዛይን እየሠራሁ እገኛለሁ፡፡ ከአዲስ አበባ እስከ ሐዋሳ 270 ኪሎ ሜትር ነው፡፡ መቂ በሁለቱ ከተሞች አማካይ ቦታ ላይ ትገኛለች፡፡

ሪፖርተር:- ሆቴሉን ፋይናንስ የሚያደርገው ማነው? የባንክ ምንጮችን ነው የምትጠቀሙት ወይስ የራሳችሁን ትጠቀማላችሁ?

ኢንጂነር ዘለቀ:- የራሳችንም አለ፡፡ በምንሠራቸው ሥራዎች አንዱ አንዱን እንዲደግፍ ይደረጋል፡፡ ባንኮችም ፋይናንስ ያደርጉናል፡፡ አሁን ባለው አቢሲኒያ፣ ኦሮሚያ፣ ኅብረት ባንክ፣ ብርሃንና ዳሽን ባንክ ጥሩ ግንኙነት አለን፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታ ብድር ተቸግረን አናውቅም፡፡

ሪፖርተር:- የኮንስትራሽን ኩባንያው ምን ዓይነት ሥራዎችን ነው የሚሠራው?

ኢንጂነር ዘለቀ:- የተቋቋመው በ2001 ዓ.ም. ሲሆን፣ በዚያው ዓመት ሥራ ጀምሯል፡፡ ጎንደር ፒንና ኪነ ሎጅን ሠርተናል፡፡ ባህር ዳር ሐይቅ ደስ የሚልና ውብ ቦታ ነው፡፡ ሎጁም የዚያኑ ያህል ውብ ነው፡፡ ቆቦ ወረዳ ጤና ጣቢያ ሠርተናል፡፡ ከጤና ጣቢያ በተጨማሪ ትምህርት ቤቶችና ቤተመጻሕፍት ሠርተን አስረክበናል፡፡  በሄድንበት ቦታ ኅብረተሰቡ የሚቸግረውን ሠርተን እንሰጣለን፡፡ ለምሳሌ አርሲ ነገሌ ላይ መንገድ ሠርተን ሰጥተናል፡፡ መንገድ ሠርተን ስናስረክብ የአርሲ ነገሌ አካባቢ ቤተ መጻሕፍት ስላልነበረው ሠርተን ሰጥተናል፡፡ ቦረና ውስጥ በጃፓን የልማት ተራድኦ ድርጅት ከፍተኛ የገበያ ማዕከል አሠርተናል፡፡ እኛ ደግሞ በበኩላችን የገበያ ማዕከሉን ኮምፒውተራይዝድ አድርገናል፡፡

ሪፖርተር:- ምን ያህል ሠራተኛ አላችሁ? ለሠራተኞቻችሁ ምን የተለየ ነገር ታደርጋላችሁ?

ኢንጂነር ዘለቀ:- 46 የሚሆኑ ሠራተኞች አሉን፡፡ እነዚህ ፕሮፌሽናል ናቸው፡፡ በንፅፅር የተሻለ ደሞዝ እንከፍላለን፡፡ ከዚያ በተጨማሪ ማንኛውም ሠራተኛ ሲቀጠር የሕክምናና የሕይወት ኢንሹራንስ ይኖረዋል፡፡ ኢንሹራንሱ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለቤተሰቦቹም ጭምር የሚያገለግል ነው፡፡ ራቅ ወዳለ ቦታም ሲሄድ ካምፕ ይዘጋጃል፡፡ ሙሉ ወጪ ነው የምንሸፍነው፡፡

ሪፖርተር:- በቅርቡ ከኢትዮጵያ መድህን ድርጅት ጋር ለሠራተኞቻችሁ ኢንሹራንስ ገብታችሁ ፊርማም አኑራችኋል? መነሻችሁ ምንድነው?

ኢንጂነር ዘለቀ:- እንደነገርኩህ ይህንን ነገር ቀድመን እናደርጋለን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከአሥር ሚሊዮን በላይ ሠራተኞች አሉ፡፡ የመንግሥትን ጨምሮ፡፡ እነዚህ ሁሉ የሕክምና የሕይወት፣ ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው መድህን ቢገባላቸው ብዙ ዓይነት ለውጥና መነቃቃት ይኖራል የሚል እምነት አለን፡፡ ሠራተኞቹ ሥራቸውን በአግባቡ ይሠራሉ፣ ቤተሰቦቻቸውም በነሱ ሞት ምክንያት እንደማይበተን ሲያስቡ ጥሩ ስሜት ይሰማቸዋል፡፡ እናም ሙሉ ኢንሹራንስ ነው የገባንላቸው፡፡ ሠራተኞቻችን በሥራ ላይ ቢሆኑም ባይሆኑም ኢንሹራንሱ ይሸፈናል፡፡ የሕክምናም ይሁን የሞት ኢንሹራንሱ ይሸፈናል፡፡

ሪፖርተር:- እርሶ ከቢዝነስ ሥራ በተጨማሪ በአንድነት ለፍትሕና ለዲሞክራሲ ፓርቲ አመራር ነዎት? በተቃዋሚ ፖለቲካ ውስጥ እንደመሆንዎ ቢዝነስዎት ላይ ተፅዕኖ ደርሶብዎት ያውቃል? ይህንን የጠየኩዎት በተቃዋሚ ጎራ የተሠለፉ አካላት ከገዥው ፓርቲ ተፅዕኖ እንደሚደርስባቸው ስለሚገልጹ ነው?

ኢንጂነር ዘለቀ:- ትልቁ ፈተና ይኼ ነው፡፡ እስካሁን ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ ሁለት የመንግሥት ሥራዎችን ብቻ ነው የሠራሁት፡፡ እንደውም የተጀመረ አስቁመውኛል፡፡ ምክንያቱም ጤና ጣቢያ ገብቼ ጊዚያዊ የበጐ አድራጐት አስተዋጽኦ አድርጌ ነበር፡፡ በመሆኑም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱን ሊረዳን ይችላል ብለው እንድገነባ ታስቦ ነበር፡፡ በዚያ ወቅት የ2002 ዓ.ም. ምርጫ ነበርና በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የምርጫ ክርክር ከገዥው ፓርቲ ሰዎች ጋር ስከራከር ታይቼ ነበር፡፡ የጨረታውን ሰነድ ስገዛ ሁለት ጊዜ ካሸነፍክ እናሳውቃለን ተባልኩ፡፡ ጨረታውን እንደተሰረዘ ተረዳሁ፡፡  እኔ የምሠራው ለውጭ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው፡፡ የመንግሥት ሥራ ማግኘት በጣም ከባድ ነው፡፡ የኔ ችግር ድርጅቴ በስሜ መሆኑ ነው  ‹‹ዘለቀ ረዲ ኮንስትራክሽን›› ተብሎ ነው የሚጠራው፡፡ ትልቅ ጫና ነው ያለው፡፡ ነገር ግን ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ችግር የለባቸውም፡፡ ጎርጎራ ላይ የሠራሁት የኔዘርላንዳውያን ነው፡፡ ከዚያም የሠራሁት ለውጭ ድርጅቶች ነው፡፡ ከመንግሥት ሥራ ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ የውጭ ድርጅቶች ደጋፊ ሁን ተቃዋሚ ግድ የላቸውም፡፡ ሌላው ነገር እንዳያጠቁህ ሕግ መጠበቅ አለብህ፡፡ ቀዳዳ መፈጠር የለበትም፡፡ እኔ ሕግ ጠብቄ ነው የምሠራው፡፡ ሌላው ተቃዋሚ ከሆንክ ጥቃት ደርሶብህ ስታመለክት ፍትሕ አታገኝም፡፡ በዚህ መልኩ እኔ 400 ሺሕ ብር ተበልቼአለሁ፡፡ ደረቅ ቼክ ሰጥተውኝ ብሬ ተበልቷል፡፡ ለሕግ አጣሪ ኮሚቴ ሰጥቼ ከአምስት ዓመት በኋላ ታይቷል ውሳኔውን እየጠበኩ ነው፡፡

ሪፖርተር:- ይኼ ከመግሥት ወገን አለ ያሉት ችግር ነው፡፡ ከእርሶ ጋር አብረው ያሉ በተቃዋሚ ፓርቲ ሥራ ባልደረቦችዎ እንዴት ነው የሚታዩት?  ለተቃውሞ ጎራ ሰዎች ቢዝነስ መሥራት አስቸጋሪ ነው እየተባለ እርሶ ቢዝነስ ሲያሳሂዱ እንዴት ነው የሚመለከትዎት?

ኢንጂነር ዘለቀ:- ለምሳሌ እኔ የኮንዶሚኒየም ግንባታ የሚባል ተሰጥቶኝ አያውቅም፡፡   እየጠሩ ነው የሚሰጡት፡፡ እኔን አያውቁኝም፡፡ ስሜ ግን መዝገባቸው ላይ አለ፡፡ አንተ ለፍተሕ እንደምታገኝ አያውቅም፡፡ መንግሥት ሰጠው ምናምን ሊሉ ይችላሉ፡፡ ትክክለኛው ነገር ግን ከመንግሥት ሥራ አለማግኘታችን ነው፡፡ እውነቱ ያገኘነውን መቀማታችን ነው፡፡ ለምሳሌ ስኳር ኮርፖሬሽን ተወዳድረን አሸንፈን ነበር፡፡ ጎንደር ስብሰባ ላይ በመታየቴ ተሰርዟል፡፡ የኛ አገር ፖለቲካ በእውቀት ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ ግምት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

ሪፖርተር:- ችግር ሲፈጠርባችሁ፣ ከፍተኛ የመንግሥት አካል ችግሩን እንዲፈታላችሁ መመርያ እንዲሰጥ ጥያቄ አቅርባችኋል?

ኢንጂነር ዘለቀ:- ይገርምሃል የኔ እናት በጣም ጎበዝ ገበሬ ናት፡፡  እኔ ያደኩበት ወረዳ ሄደህ አንድ ጎበዝ ገበሬ ሴት ጠቁሙኝ ብለህ ብትጠይቅ ሁሉም ይናገራል፡፡ የኔ እናት ነች፡፡ የኔ እናት ግን ጎበዝ ገበሬ ተብላ ተሸልማ አታውቅም፡፡ ብቻዋን ታርሳላች ብቻዋን ቤት ትሠራለች፡፡ ጎበዝ ተብላ እውቅና ተሰጥቷት ግን አያውቅም፡፡ አንድ ጊዜ መሬቷን ተቀምታ ወረዳው ወ/ሮ ፀሐይ እንዲህ ብለው ከሰዋልና መልስ ስጧት ብለው መለሱ፡፡ ይህ ትክክል ነው? የበደለህን አካል ከፍ ብለህ ብትከስ ከፍ ተብሏል ተብሎ አቤቱታ የቀረበለት አካል መልሶ ወደ መጀመሪያው አካል ይመልስሃል፡፡ ይህ አግባብ ሊሆን አይችልም፡፡ እኔ አላግባብ ዱከም ላይ ዕቃዬ ተወስዶ ዕቃዬ እንዲታገድልኝ ለፍርድ ቤት አቤት አልኩ፡፡ አልተደመጥኩም ከፍ ላለው አቤቱታየን አቀረብኩ፡፡ ወደ ቀድሞው ቦታ መልሰው አነሱ እኛን ከሰህ የት ትገባለህ ነው ያሉኝ፡፡ በናንተ በኩል ይፈጸም ተብሎ ወደ ታች የሚመለስ ከሆነ እንዴት መፍትሄ ይገኛል፡፡ ይህ አስቸጋሪ ነገር ነው፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment