Sunday, December 8, 2013

የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊው ከእህትና ከወንድማቸው ጋር በድጋሚ ክስ ተመሠረተባቸው


Ethiopian Reporter
ከግንቦት ወር 1983 ዓ.ም. እስከ የካቲት ወር 2005 ዓ.ም. ድረስ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት የአገር ውስጥ ኃላፊ የነበሩት አቶ ወልደ ሥላሴ ወልደ ሚካኤል፣ እህትና ወንድማቸው የተካተቱበት ድጋሚ ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

በእነ አቶ መላኩ ፈንታ የክስ መዝገብ 141352 ተካተው ክስ ተመሥርቶባቸው የነበሩት አቶ ወልደ ሥላሴ፣ አቶ ዘርዓይ ወልደ ሚካኤልና ወ/ሮ ትርሀስ ወልደ ሚካኤል ከሚባሉ ወንድምና እህታቸው እንዲሁም የቅርብ ጓደኛቸው መሆናቸው የተገለጹ አቶ ዱሪ ከበደ ጋር ኅዳር 23 ቀን 2006 ዓ.ም. የተጻፈ ክስ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ኅዳር 26 ቀን 2006 ዓ.ም. ቀርቦባቸዋል፡፡

ክሱን የመሠረተው የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ በአጠቃላይ 12 ክሶችን ያቀረበ ቢሆንም፣ አምስቱ ክሶች በአቶ ወልደ ሥላሴ ላይ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ክሶች በጋራ የቀረቡ ናቸው፡፡

በአቶ ወልደ ሥላሴ ላይ በዋናነት በመጀመርያው ክስ ላይ የቀረበው የተጠረጠሩበት ወንጀል ‹‹Terrorism in Ethiopia and the Horn of Africa›› በሚል ያሳተሙትን መጽሐፍ በሚመለከት ሲሆን፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ በየነ ገብረ መስቀልን የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዙ በማድረግ፣ በበላይነት የሚመሯቸው ድርጅቶች መጽሐፉን ለማሳተም ስፖንሰር እንዲያደርጓቸው ማድረጋቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡


አቶ ወልደ ሥላሴ ከአቶ በየነ ጋር በሥራ አጋጣሚ ያላቸውን ቀረቤታና ትውውቅ በመጠቀም፣ የመጽሐፋቸውን ረቂቅ ተመልክተው አስተያየት እንዲሰጧቸው በማድረግ፣ ስለሕትመቱም በማወያየትና መጽሐፉ በመሥርያ ቤታቸው የተዘጋጀ አስመስለው በመንገር አቶ በየነ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዙ በማድረግ ብርሃንና ሰላም፣ ቦሌና አርቲስቲክ ማተሚያ ቤቶች ስፖንሰር እንዲሆኑዋቸው ማድረጋቸውን የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

አቶ ወልደ ሥላሴ ከኢትዮ ቴሌኮም የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አማረ አምሳሉ ተፈቅዶ በተሰጣቸው 385,226 ብር በሜጋ ማተሚያ ቤት ያሳተሙትን መጽሐፍ ለድርጅቱ መስጠት ሲገባቸው ሸጠው መጠቀማቸውን፣ የቦርድ አባል በሆኑባቸው የኢትዮጵያ አትክልትና ፍራፍሬ ገበያ አክሲዮን ማኅበርና ሙገር ሲሚንቶ ኢንተርፕራይዝ፣ ኃላፊዎቹ መጽሐፉን እንዲገዙ በማድረግ ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም ሙስና መፈጸማቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

“Terrorism in Ethiopia and the Horn of Africa” የተሰኘው የአቶ ወልደ ሥላሴ መጽሐፍ ለአልሳም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለቤት አቶ ሳቢር አርጋው፣ ጌታስ ትሬዲንግ ፒኤልሲ፣ አቶ ተክለ ብርሃን አምባዬ፣ ነፃ ፒኤልሲ፣ ካንትሪ ትሬዲንግ፣ አኪር ኮንስትራክሽን፣ ኪሊማንጃሮ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግና ሐበሻ ካፒታል ሰርቪስን ጨምሮ 26 ግለሰቦችና ድርጅቶች ከ25 እስከ 1,500 መጽሐፍትን እንዲገዙ በማድረግ፣ ገንዘቡን ከተቀበሉ በኋላ መጽሐፉን ሳይሰጧቸው ለግል ጥቅም በማዋላቸው፣ ዋጋ ያለውን ነገር ያለ ክፍያ ማግኘት የሙስና ወንጀል መከሰሳቸውን የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ ያብራራል፡፡

አቶ ወልደ ሥላሴ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት የአገር ውስጥ ኃላፊነታቸውን በመጠቀም፣ ለአንዲት ግለሰብ የመሥሪያ ቤታቸውን ተሽከርካሪ ነዳጅ በመሙላት ወደ ቁልቢ ገብርኤል እንድትሄድበትና የመሥሪያ ቤታቸውን ሠራተኛ በመመደብ ለግለሰቧ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረጋቸውን፣ ለግለሰቧ የግል ሥራ የመሥሪያ ቤታቸውን ሠራተኞች በመመደብ ጉዳይ እንዲያስጨርሱ በማድረጋቸው፣ ሥልጣንን ያላግባብ የመገልገል የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡

ቀኑና ወሩ በትክክል በማይታወቅበት በ2003 ዓ.ም. መጨረሻና በ2004 ዓ.ም. መጀመርያ አካባቢ 65 ሺሕ ብር ዋጋ ያለው ሴራሚክስ ከአቶ ሳቢር አርጋው ገዝተው እንዲያቀርቡላቸው በስልክ በማዘዝ ሥልጣናቸውን ያላግባብ መጠቀማቸውም በክሱ ተካቷል፡፡ ከ2001 ዓ.ም. እስከ 2005 ዓ.ም. ድረስ አሳትመው ከሸጧቸው መጻሕፍት 496,159 ብር ለመንግሥት አሳውቀው ግብር መክፈል ሲገባቸው ሕግን በመጣስ አለመክፈላቸውንም የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ ይጠቁማል፡፡

አቶ ወልደ ሥላሴ የገነቡትን ባለ ሦስት ፎቅ የመኖሪያ ቤት ሕንፃ ከመኖሪያ ቤትነት ውጭ ለሆነ አገልግሎት እንዲውል በማድረግና ከፋፍለው በማከራየት በወር 50 ሺሕ ብር የሚያገኙ መሆኑንና ይኼንኑ ሕንፃ ለሁለተኛ ተከሳሽ ወንድማቸው አቶ ዘርዓይ ወልደሚካኤል ሚያዝያ 25 ቀን 2004 ዓ.ም. ሕጋዊ ውክልና በመስጠት፣ የ14 ወራት ኪራይ 790 ሺሕ ብር የሰበሰቡ ቢሆንም፣ ለመንግሥት መክፈል የነበረባቸውን የ2004 ዓ.ም. እና 2005 ዓ.ም. ግብር 126,797 ብር አለመክፈላቸውን፣ ወንድማማቾቹ በጋራ በተጠቀሱበት ስድስተኛ ክስ ተጠቁሟል፡፡ በ2004 ዓ.ም. እና በ2005 ዓ.ም. ካገኙት ገቢ 119,062 ብር የተርን ኦቨር ታክስ ግብርም አለመክፈላቸው በክሱ ተጠቅሷል፡፡

አቶ ወልደ ሥላሴ ከግንቦት ወር 1983 ዓ.ም. እስከ የካቲት ወር 2005 ዓ.ም. ድረስ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት የአገር ውስጥ ኃላፊ ሆነው ሲሠሩ፣ ከ1600 ብር እስከ 6000 ብር ድረስ ይከፈላቸው እንደነበር የሚጠቁመው የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ፣ ወንድማቸው ሁለተኛ ተከሳሽ አቶ ዘርዓይ በአገር መከላከያ ሚኒስቴር ሲሠሩ ጡረታ እስከወጡበት ግንቦት ወር 1995 ዓ.ም. ድረስ 532 ብር ገቢ ያገኙ እንደነበር ይገልጻል፡፡

ሦስተኛ ተከሳሽና እህታቸው ወ/ሮ ትርሀስ ወልደሚካኤል ሥራ ያልነበራቸው መሆኑን የሚገልጸው የኮሚሽኑ ክስ፣ አራተኛው ተከሳሽና ከአቶ ወልደ ሥላሴ ጋር የረጅም ጊዜ ትውውቅ የነበራቸውና የቅርብ ጓደኛ መሆናቸው ለተገለጸው አቶ ዱሪ ከበደና ቤተሰቦቻቸው፣ የአቶ ወልደ ሥላሴ የሆነውና በአቶ ዘርዓይና በወ/ሮ ትርሀስ ስም ተይዞ የነበረ ንብረት ማዛወራቸው በክሱ ተገልጿል፡፡ ይኼም የተደረገው አቶ ወልደ ሥላሴና ወ/ሮ ትርሀስ የየራሳቸውን ሙሉ ውክልና ለወንድማቸው አቶ ዘርዓይ ያስተላለፉ በማስመሰል መሆኑን ክሱ ይጠቁማል፡፡

አቶ ወልደ ሥላሴ በኃላፊነት ላይ በነበሩበት አጋጣሚ የያዙት ሀብት እንዳይደረስበት ለማድረግ ለወንድማቸው ሙሉ ውክልና በመስጠት፣ እንዲሁም ምንም ገንዘብ ሳይሰጣጡ ውል በመፈራረም በወንድማቸውና በእህታቸው ስም በተለያዩ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች፣ ከገቢያቸው ጋር የማይመጣጠን ገንዘብ በማስቀመጥና ሀብት በማፍራት በመቀሌ፣ በአክሱምና በአዲስ አበባ ውስጥ ቦታ በመግዛት፣ ሉሲ የእርሻ ልማት የተባለ የእርሻ ኢንቨስትመንት በአፋር በማቋቋምና ለአቶ ዱሪ ውክልና በመስጠት፣ ኩዳ የተባለ የእርሻ ልማት ኢንቨስትመንት በሁለት እህቶቻቸው ስም በማቋቋም፣ ኤክስካቫተርና የግል ተሽከርካሪ በመግዛት፣ በወጋገንና በአንበሳ ባንኮች ከፍተኛ ገንዘብ ማስቀመጣቸውን የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ ያብራራል፡፡

የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክሱን ያረጋግጡልኛል ያላቸውን 40 የሰው ምስክሮችና 54 የሰነድ ማስረጃዎችን ከክሱ ጋር አያይዞ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል፡፡

የተመሠረተባቸው ክስ በችሎት ከተነበበላቸው በኋላ አስተያየት ካላቸው የተጠየቁት ተከሳሾቹ፣ ጊዜ ተሰጥቷቸው ያላቸውን አስተያየት እንዲያቀርቡ እንዲታዘዝላቸው ከጠየቁ በኋላ፣ ከአቶ ወልደ ሥላሴ በስተቀር ሦስቱም ተከሳሾች ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ የሁለት ዓመት ሕፃን ልጃቸውን ለ70 ዓመት አዛውንት እናታቸው ሰጥተው መቅረባቸውን የወ/ሮ ትርሀስ ጠበቃ በመግለጽ በተለይ የእሳቸው የዋስትና ጉዳይ እንዲታይላቸው ጠይቀዋል፡፡

ተከሳሾቹ ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ በሚመለከት አስተያየቱን የተጠየቀው የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ በሰጠው ምላሽ፣ ተከሳሾቹ የተጠቀሰባቸው የወንጀል ሕግ አንቀጽ ከአሥር ዓመታት በላይ የሚያስቀጣ በመሆኑ፣ ጥያቄያቸው ተቀባይነት እንደማይኖረው በመጠቆም ጥያቄው ውድቅ እንዲሆን ለፍርድ ቤቱ አመልክቷል፡፡

ፍርድ ቤቱም የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን መቃወሚያ በመቀበል፣ የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ፣ ተከሳሾቹ በክሱ ላይ ያላቸውን አስተያየት ለመቀበል ለታህሳስ 7 ቀን 2006 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ክሱ ግልጽ እንደሆነም በመናገር የክስ መግለጫ እንደማያስፈልገውና በመደበኛ እንደሚታይ አሳውቋል፡፡  
 http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment