Thursday, July 4, 2013

ዶክተር ያዕቆብ አስታጥቄ በአሜሪካ ምርጡ የምሕንድስና መምህር ተብለው ተሰየሙ

ኢትዮጵያዊው የምሕንድስና ፕሮፌሰር ዶ/ር ያዕቆብ አስታጥቄ በአሜሪካ የ2013 ምርጡ የምሕንድስና መምህር ተብለው ተሰየሙ፡፡
በሞርጋን ስቴት ዩኒቨርሲቲ የምሕንድስና መምህር የሆኑት ዶ/ር ያዕቆብ፣ በአሜሪካ 240 የምሕንድስና ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ካሉት 27 ሺሕ መምህራን መካከል ምርጡ አስተማሪ ተብለው መሰየማቸውን ዲንግ ማጋዚን በድረ ገጹ ዘግቧል፡፡

ዶ/ር ያዕቆብ አሜሪካ በሚገኘው ሞርጋን ስቴት ዩኒቨርሲቲ በኤሌክትሪካልና በኮምፒውተር ኢንጀነሪንግ ፋኩሊቲ ሙሉ አባልና መምህር ሲሆኑ፣ የቅድመ ምረቃ ፕሮግራም ተባባሪ ሊቀመንበር ኾነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ በአገር አቀፍ፣ በአህጉር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ አንቱ ያሰኛቸውን በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ 35 ያህል የጥናት ወረቀቶችንና የምርምር ጽሑፎችን አቅርበዋል፡፡

ምርጡ የምሕንድስና መምህር ባለፉት አስር ዓመታት ወደ አገራቸው በመመላለስ በአዲስ አበባና በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች የድኅረ ምረቃ ተማሪዎችን በማስተማርና የተለያዩ ትምህርታዊ ኮንፈረንሶችን በማዘጋጀት ይታወቃሉ፡፡ ምሁሩ የእውቁ ኢትዮጵያዊ የጃዝ ሙዚቃ አቀናባሪና የሙዚቃ መምህር ሙላቱ አስታጥቄ ወንድም ናቸው፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment