Monday, June 17, 2013

የሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎች የፍርድ ቤት ውሎ በስድብና በእንባ ታጅቦ ቀጥሏል

‹‹የተወነጀልኩበት ክስ ትክክል ነው ወንድሜ ጉድ ሠርቶኛል››   የተጠርጣሪ መርክነህ ወንድም ብርሃኑ አለማየሁ
‹‹ሰብዓዊ መብታችን ተገፎ ውኃ እየተደፋብን በጥፊ እንመታለን›› አንዲት ተጠርጣሪ
የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከፍተኛ ባለሥልጣናትን፣ ነጋዴዎችን፣ ትራንዚተሮችንና ደላሎችን ያካተተው የከፍተኛ የሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎች ክርክር፣ በስድብና በእንባ ታጅቦ ሰኔ 5 እና 6 ቀን 2005 ዓ.ም. ቀጥሎ ውሏል፡፡ 

በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል ችሎት ቀርበው የነበሩት የባለሥልጣኑ የውስጥ ኦዲት ዳይሬክተር አቶ ንጉሴ ክብረት፣ የመረጃ መረብ ክፍል ኃላፊ አቶ ምሳሌ ወልደ ሥላሴ፣ የአዳማ ጉምሩክ ፈታሽና ትመና ኦፊሰር አቶ ጥጋቡ ግደይ፣ የሐረር ከተማ ነዋሪና ነጋዴ የሆኑት ወ/ሮ ሶፊያ ሱሌይማንና የብሥራትና ናትራን ድርጅቶች ባለቤት የሆኑት አቶ ባሕሩ አብርሃ ናቸው፡፡
ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር በማዋል የሙስና ወንጀል መፈጸም አለመፈጸማቸውን በምርመራ በማጣራት ላይ የሚገኘው የፌደራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ቡድን፣ በዕለቱ በቀረቡት ተጠርጣሪዎች ላይ የሠራውን የምርመራ ክንውን ለችሎቱ አቅርቧል፡፡
የብሥራትና ናትራን ድርጅቶች ባለቤት አቶ ባሕሩ የተጠረጠሩት በቫት ማጭበርበር ተመሥርቶባቸው የነበረውን ክስ ከባለሥልጣኑ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመመሳጠር እንዲቋረጥ በማድረጋቸውና ለመንግሥት ይከፍሉት የነበረውን ከፍተኛ ገቢ ዝቅ በማድረግ ጉዳት በማድረሳቸው መሆኑን ተናግሯል፡፡

በባለሥልጣኑ የውስጥ ኦዲት ዳይሬክተር አቶ ንጉሴ ከነጋዴዎች ጋር በመመሳጠር ለመንግሥት ገቢ መሆን የሚገባውን የታክስና ቀረጥ ገቢ ዝቅ ማድረጋቸውን መርማሪ ቡድኑ ጠቁሟል፡፡ የመረጃ መረብ ክፍል ኃላፊው አቶ ምሳሌም የታክስ መረጃዎችን በማዛባት በመንግሥት የታክስና የቀረጥ ገቢ ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ገልጿል፡፡ ቡድኑ በሁሉም ተጠርጣሪዎች ቤት በብርበራ የተገኙ ሰነዶችን የመለየት ሥራ እየሠራ መሆኑን፣ ከአዲስ አበባ ውጪ ወደ አዳማ፣ ሚሌና አዋሽ የጉምሩክ መፈተሻ ጣቢያዎች የምርመራ ቡድን ልኮ ማስረጃ እየሰበሰበ መሆኑንም አክሏል፡፡
ቀረጥና ታክስ አልከፈሉም ተብለው በተጠረጠሩ ድርጅቶች ላይ የኦዲት ምርመራ ማድረጉንና የተቋረጡ የክስ መዝገቦችን መሰብሰቡን ገልጾ፣ ቀሪ ሥራዎች እንዳሉት በመዘርዘር ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ችሎቱን ጠይቋል፡፡
የተጠርጣሪ ጠበቆች መርማሪ ቡድኑ የጠየቀውን የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተቃውመዋል፡፡ ምክንያቶቻቸውም መርማሪ ቡድኑ በደንበኞቻቸው ላይ ያቀረበው ዝርዝር የምርመራ ሁኔታ በሌለበትና ማን በምን እንደተመረመረና በማን ላይ ምን እንደቀረው ግልጽ የሆነ ነገር ስለሌለ፣ የደንበኞቻቸው የዋስትና መብት ተጠብቆ እንዲለቀቁና በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ጠይቀዋል፡፡
አዳማ ውስጥ የንግድ ድርጅት እንዳላቸው የተገለጸውና ነዋሪነታቸው ሐረር ከተማ ውስጥ የሚኖሩት ወ/ሮ ሶፊያ ሱሌይማን የተባሉ ነጋዴ ከተቀመጡበት ተነስተው እጃቸውን ወደ ኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን በማመልከት፣ ‹‹ሌቦች፣ ውሸታሞች፣ በውሸት እንዴት ሰው ይወነጀላል? ሰው ተዋወቅሽ ተብዬ! ሰው መተዋወቅ አይቻልም እንዴ? ሀብታም ነች በሚል! እኔ እኮ በኪራይ ቤት የምኖር የልጆች እናት ነኝ፡፡ እያንዳንድሽ በእኔ የደረሰ ይደርስብሻል፡፡ በሐሰት ተናገሪ እያሉኝ ነው፤›› በማለት ሲናገሩ ሦስቱም የችሎቱ ዳኞች ‹‹አረጋጓት›› በማለታቸው ፖሊሶች ይዘዋቸው ከችሎት ወጥተዋል፡፡
ወ/ሮ ሶፊያ የተጠረጠሩት ከአዳማ ወደ አዲስ አበባ የሚገባ ዕቃ እንዳይቀረጥና ኃላፊዎችንና ነጋዴዎችን በማገናኘት፣ ጉቦ በማቀባበልና የራሳቸው ዕቃም ሳይፈተሽ እንዲያልፍ አድርገዋል በሚል መሆኑን መርማሪ ቡድኑ ለችሎቱ ማስረዳቱ ይታወሳል፡፡
ወ/ሮ ሶፊያ ተረጋግተው ወደ ችሎቱ ሲመለሱ ሐሳባቸውን በጠበቃቸው በኩል እንዲናገሩ ችሎቱ በማዘዙ፣ ጠበቃቸው እንዳሉት፣ ወ/ሮ ሶፊያ የተጠረጠሩበትን ወንጀል አያውቁትም፡፡ ችሎቱ ተረጋግተዋል በሚል ጠበቃቸው ከተናገሩት ውጪ ቀረ የሚሉት ሐሳብ ካላቸው እንዲናገሩ ወ/ሮ ሶፊያ ቢፈቅድላቸውም፣ ‹‹አቦ እኔ ምንም የፈጸምኩት የለም፡፡ አጥፍታለች ካላችሁ የፈለጋችሁትን ዕርምጃ መውሰድ ትችላላችሁ፤›› በማለት መልስ ሰጥተዋል፡፡ ጠበቃቸው ግለሰቧ የሐረር ነዋሪ በመሆናቸው ባህሪያቸውና ባህላቸው መሆኑን ፍርድ ቤቱ ይረዳላቸዋል የሚል ግምት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ ወ/ሮ ሶፊያ የተናገሩት ወደ ሌላ ሳይመነዘር እሳቸው (ጠበቃው) ብቻ ያሉት እንዲመዘገብላቸውም ጠይቀዋል፡፡ ወ/ሮ ሶፊያ ንግግራቸው በእንባ የታጀበ ነበር፡፡
ሌላው በእነ አቶ መላኩ ፈንታ የምርመራ መዝገብ እንዲካተቱ ፍርድ ቤቱ ቢያዝም ተጠርጣሪው የወላይትኛ ቋንቋ ተናጋሪ በመሆናቸው ከሰኔ 4 ቀን ወደ ሰኔ 5 ቀን 2005 ዓ.ም. በአዳር እንዲቀርቡና በአስተርጓሚ እንዲከራከሩ የተደረጉት፣ የባለሥልጣኑ ዓቃቤያነ ሕግ ምክትል ዳይሬክተር አቶ መርክነህ አለማየሁ ወንድም ተጠርጣሪ ብርሃኑ ዓላማየሁ ናቸው፡፡
አቶ ብርሃኑ የተጠረጠሩት የወንድማቸው ገንዘብ የሆነ 1.3 ሚሊዮን ብር ቀብረው ተገኝተዋል በሚል መሆኑን መርማሪ ቡድኑ ለችሎት ማስረዳቱ ይታወሳል፡፡ በወላይታ ሶዶ ነዋሪ መሆናቸውን የገለጹት አርሶ አደር ብርሃኑ፣ ‹‹እኔ ምንም በማላውቀው ነገር ወንድሜ ጉድ ሠራኝ፡፡ የተወነጀልኩበት ክስ እውነት ነው፤ የእኔ ችግር አይደለም የመርክነህ ነው፤ ገንዘቡን አንተ ጋ አስቀምጥልኝ፤ ቤት ሸጬ ነው ብሎ ጉድ ሠራኝ፤›› በማለት እያለቀሱ በአስተርጓሚ ገልጸዋል፡፡ የተያዙትም ብሩን ቤት ውስጥ ቀብረው ለእርሻ ሲወጡ መሆኑንም አልደበቁም፡፡
የዘጠኝ ልጆች አባት መሆናቸውንና የ11 ቤተሰብ አስተዳዳሪ እንደሆኑ የገለጹት አቶ ብርሃኑ፣ ከጉልበታቸው ሸብረክ ብለው ሁለት እጆቻቸውን ወደ ላይ ከፍ በማድረግ ‹‹መርክነህ የሥራውን ይስጠው ችሎቱ ይቅርታ ያድርግልኝ፤›› በማለት ሲያለቅሱ ፖሊስ እንዲያረጋጋቸው ተደርጓል፡፡ ችሎቱም፣ ‹‹ምን እንዲደረግልህ ነው የምትፈልገው?›› በማለት ሲጠይቃቸው፣ የዋስትና መብታቸው እንዲፈቀድላቸው ጠይቀው፣ ልብስ እንደሌላቸውና ከወላይታ እስከ አዲስ አበባ ለመመላለስ የአንድ ጊዜ መጓጓዣ 600 ብር በመሆኑ፣ ቤተሰብም ሊጠይቃቸው እንደማይችልና ምግብም እንደሌላቸው አስታውቀዋል፡፡
የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን በእነ መሐመድ ኢሳ የምርመራ መዝገብ ያሉትን ተጠርጣሪዎች ማለትም መሐመድ ኢሳ፣ ሰመረ ንጉሴ፣ ዘሪሁን ዘውዴ፣ ማርሸት ተስፋዬ፣ ሙሉቀን ተስፋዬና ፍሬሕይወት ጌታቸው ላይ የሠራውን የምርመራ ክንውን ለችሎቱ አሰምቷል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ የባለሥልጣኑ የአዳማ ቅርንጫፍ ሠራተኞችና የትራንዚት ባለቤቶች (ወ/ሮ ፍሬሕይወት) እና ደላሎች መሆናቸውን ገልጾ፣ ከኃላፊዎች ጋር በመመሳጠር ከጂቡቲ ወደ አዲስ አበባ የሚገባ ዕቃ እንዳይፈተሽ በጉቦ በማሳለፍ በመንግሥት ገቢ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን ለችሎቱ አስታውቋል፡፡ በመሆኑም ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ማፍራታቸውን አክሎ በብርበራ የተያዙ ሰነዶችን የመለየት ሥራ መሠራቱን፣ የተሰበሰቡ የኤሌክትሮኒክስ መሣርያዎችን ለባለሙያ ለማስተንተን መስጠቱን፣ ከአዲስ አበባ ውጪ በሚሌና በአዋሽ ጉምሩክ መፈተሻ ጣቢያዎች መርማሪ ቡድን መላኩን አስታወቆ፣ ቀሪ ሥራዎች እንዳሉት በማስረዳት ተጨማሪ የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ጠይቋል፡፡
የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆችም እንደሌሎቹ ተጠርጣሪዎች ጠበቃዎች ሁሉ የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜውን በመቃወም ደንበኞቻቸው በዋስ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ተጠርጣሪዎች ያቀረቡትን የዋስትና መብት በመቃወም ዋስትና ቢፈቀድላቸው ቀሪ ሰነዶችን ሊያሸሹ እንደሚችሉ፣ ምስክሮች ሊያባብሉና ሊያጠፉ እንደሚችሉ፣ እነሱም ሊጠፉ እንደሚችሉ በመግለጽ የተቃውሞውን ምክንያት አስረድቷል፡፡
የአቶ መርክነህ ወንድምን በሚመለከት መርማሪ ቡድኑ ለችሎቱ ባቀረበው ማመልከቻ፣ ‹የእምነት ቃላቸው በወንጀል ሕግ ቁጥር 35 መሠረት የእምነት ቃል ሆኖ ይመዝገብልኝ፤›› ቢልም ፍርድ ቤቱ፣ ‹‹ይኼ ችሎት የእምነት ቃል መቀበያ አይደለም፡፡ የእምነት ቃል የሚቀርብበት ቦታና ጊዜ አለው፤›› በማለት ማመልከቻውን ውድቅ አድርጐበታል፡፡ ቡድኑ በአቶ ብርሃኑ የዋስትና ጥያቄ ላይ ባቀረበው መቃወሚያ ምርመራው አዲስ መሆኑን፣ ቢለቀቁ በሚኖሩበት አካባቢ ተሰሚነት ስላላቸው በአካባቢው ያለውን ማስረጃ ሊያጠፉ እንደሚችሉ፣ ወደ አካባቢው የሄደው መርማሪ ቡድን አለመመለሱን፣ አዲስ አበባ ውስጥም ምርመራ እንደሚቀረው አብራርቷል፡፡ አቶ ብርሃኑ ያቀረቡትን የምግብና የልብስ ጥያቄ ቡድኑ እንደሚያሟላ አስረድቷል፡፡
የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት፣ የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ መርማሪ ቡድኑ ያቀረበውን የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዶ፣ ለሰኔ 19 ቀን 2005 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን ሰኔ 6 ቀን 2005 ዓ.ም. በእነ መልካሙ እንድሪስና በእነ ተመስገን ሥዩም የምርመራ መዝገብ ሥር ባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ የሠራውን የምርመራ ሥራ ለችሎቱ አቅርቧል፡፡
በአቶ መልካሙ እንድሪስ፣ በሃምሳ አለቃ ደጉ አቢቾ፣ በአቶ ዳዊት መኮንንና በወ/ሮ አልማዝ ከበደ ላይ መርማሪ ቡድኑ የሠራው የምርመራ ሥራ ከቤታቸው በምርመራ የተገኙ ሰነዶችን መለየት፣ የኤሌክትሮኒክስ መሣርያዎችን ለባለሙያ ትንተና መስጠት፣ ከአዲስ አበባ ውጪ ሚሌና አዋሽ የምርመራ ቡድን ልኮ መረጃ እያሰባሰበ መሆኑን ገልጿል፡፡ ወንጀሉ ውስብስብና በመመሳጠር የተሠራ በመሆኑ ቀሪ ሥራዎች እንዳሉት፣ የኦዲተሮችን ቃል መቀበልና የባለሙያዎች የትንታኔ ምላሽ እንደሚቀረው፣ ምንጩ ያልታወቀ ሀብትን ሕጋዊ አስመስሎ መያዝን በሚመለከት ምርመራ እንደሚቀረው በመግለጽ ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ጠይቋል፡፡
በእነ ተመስገን ሥዩም፣ ጌታቸው አሰፋ (የጋምቤላ ጉምሩክ ኃላፊ)፣ ቢኒያም ለማ፣ ስንሻው ዓለምነው፣ ደረጀ መርጊያ፣ ሥዩም ለይኩንና ኃይለ ማርያም አሰፋ ላይም መርማሪ ቡድኑ በእነ መልካሙ እንድሪስ ላይ የሠራውንና የቀረውን ሥራ ለችሎቱ በማስረዳት ተጨማሪ የ14 ቀናት ጊዜ ጠይቋል፡፡
የተጠርጣሪዎች ጠበቆችም የተጠየቀውን ተጨማሪ የ14 ቀናት ጊዜ ተቃውመዋል፡፡ ምክንያታቸውም መርማሪ ቡድኑ በደንበኞቻቸው ላይ ሁሉንም ዓይነት ምርመራ መጨረሱን፣ የኦዲትና የባለሙያ ትንታኔና የምስክሮች ቃል በመቀበል ምክንያት ደንበኞቻቸው ያለምንም ምክንያት እንዲታሰሩ ማድረግ ተገቢ አለመሆኑን ነው፡፡ በመሆኑም የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡
ወ/ሮ አልማዝ የተባሉት (የጉምሩክ ሥርዓት ማስተላለፍ ሥራ ኃላፊ) ተጠርጣሪ ጠበቃ መርማሪ ቡድኑ በእያንዳንዱ ተጠርጣሪ ላይ ለይቶ ያቀረበው የምርመራ ውጤት እንደሌለ ገልጸው፣ ወንጀል የግል በመሆኑ ተለይቶ በማን ላይ ምን እንደተሠራና ምን እንደቀረ ሊገለጽ ይገባ እንደነበር ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡
ተጠርጣሪዋ እንዲናገሩ ጠይቀው ሲፈቀድላቸው፣ ‹‹መርማሪዎች ሌሊት ይወስዱንና ልብሳችንን እንድናወልቅ ካደረጉ በኋላ ውኃ ይደፉብናል፡፡ በጥፊ እንመታለን፡፡ ለምን ሰብዓዊ መብታችን ይገፈፋል?›› በማለት እያለቀሱ ሲናገሩ፣ በችሎቱ ታድመው የነበሩ ቤተሰቦቻቸው በግልጽ ያልተሰማ ንግግርና ድምፅ በማውጣትና በማልቀስ በመጯጯኻቸው ለተወሰኑ ደቂቃዎች የችሎቱን ቀልብ ስበዋል፡፡ ዳኞችና ፖሊሶች በጋራ በመናገር ጩኸትና ለቅሶውን ካስቆሙ በኋላ፣ ችሎቱ እንደገና መጮሁ ቢደገም በችሎቱ መታደም እንደማይችሉ አስጠንቅቆ ሥራውን ቀጥሏል፡፡
መርማሪ ቡድኑ የመልስ መልስ ሲሰጥ፣ ሥራውን በትጋት እየሠራ መሆኑንና ጉዳዩ ግን ውስብስብና በመመሳጠር የተሠራ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ሊጠቃለል አለመቻሉን አስረድቷል፡፡
ምርመራ መጀመሩን ሲሰሙ በጋምቤላ አድርገው ለመሸሽና ለማሸሽ ሲሞክሩ (አቶ ተመስገን 80 ሺሕ ብር ለአቶ ጌታቸው ሰጥተው) የተያዙ መሆናቸውን፣ ምርመራው ሳይጠናቀቅ በዋስ ቢወጡ ሌላውን ማሸሻቸው ቀርቶ ራሳቸውም ሊጠፉ እንደሚችሉና ሰነድ ሊያሸሹ፣ ምስክር ሊያስፈራሩና ሊያባብሉ የሚችሉ መሆኑ ገልጾ፣ ዋስትናውን ተቃውሟል፡፡
ወ/ሮ አልማዝ ከባለሥልጣናት ጋር በመመሳጠር ከፍተኛ የሆነ የመንግሥት ገንዘብ ከቀረጥ እንዳይሰበሰብ ሕገወጥ ጥቅም በማቀባበል፣ ነጋዴዎች ሕገወጥ ሥራው እንዲፈጸምላቸው በማድረግ መጠርጠራቸውን፣ ምንጩ ያልታወቀ ሀብት አከማችተው በመገኘታቸው በምርመራ ላይ መሆናቸውንና በሚሌና በአዋሽ ጉምሩክ ጣቢያዎችም ምርመራ እያደረገ መሆኑን አስረድቷል፡፡
ሰብዓዊ መብትን በሚመለከት ወ/ሮ አልማዝ የተናገሩት ሐሰት መሆኑን፣ ተቋሙ እንደዚህ ያለ ተግባር እንደማይፈጽም፣ ተቋሙ ያልሆነ ገጽታ እንዲኖረውና ታስቦ የተደረገ መሆኑን ፍርድ ቤቱ እንዲገነዘብለት ጠይቋል፡፡ ከቤተሰብ ጋር በመደራጀት ወደ ችሎት ገብተው ታዳሚው የተለየ አመለካከት እንዲኖረው ለማድረግ የተጠነሰሰ ሴራ መሆኑንም አብራርቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ ሰብዓዊ መብትን በሚመለከት ኮሚሽኑ ራሱ የማስጠበቅ ግዴታ እንዳለበት፣ ምርመራ የሚካሄደው ንፁህ የሆኑ ንፅህናቸው እንዲታወቅ፣ ያልሆኑ እንዲታረሙ መሆኑን በማስገንዘብ ሕግን የማክበርና የማስከበር ሥራ እንዲሠራ አሳስቧል፡፡ የመብት ጥሰቱ ተፈጽሟል የሚል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ተቋሙ ምርመራ አካሂዶ እውነት ሆኖ ካገኘው ዕርምጃ ሊወስድ እንደሚገባም አስታውቋል፡፡ በመጨረሻም ተጠርጣሪዎች የጠየቁትን የዋስትና መብት ውድቅ በማድረግ ለመርማሪ ቡድኑ ተጨማሪ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል፡፡ ተለዋጭ ቀጠሮውን ለሰኔ 20 ቀን 2005 ዓ.ም. በማድረግ ችሎቱን አብቅቷል፡፡ 
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment