Monday, March 11, 2013

በሐረር ከፎቅ የተገፈተረችው የቤት ሠራተኛ ኮማ ውስጥ ነች


ጥርሷ ረግፏል፤ ጉልበቷ ተሰባብሯል ተጠርጣሪዋ ከእስር እንድትለቀቅ ተደርጓል መታሰቢያ ካሣዬ (ከድሬዳዋ) በሐረር ከተማ፣ ፈረስ መጋላ አንደኛ መንገድ በተሰኘው አካባቢ በቤት ሠራተኛነት የተቀጠረች የ12 ዓመቷ ሰሚራ አብዲ በአሠሪዋ ከፎቅ ላይ ተወረወረች፡፡ ታዳጊዋ በውርወራው ጥርሶቿ ረግፈው፣ ጉልበቷም ተሰባብሯል፡፡ ተጠርጣሪዋ ከእስር መለቀቋን ፖሊስ ተቃውሟል፡፡ በመቶ ብር የወር ደሞዝ ለመስራት ገብታ ሁለት ሳምንት እንደቆየች ነው ችግር የተፈጠረው፡፡
አሰሪዋ ሶፍያ መሃመድ መቶ ብር ጠፍቶባት ህፃኗን ወስደሽብኛል ትላታለች፡፡ ህፃኗ ሰሚራ ገንዘብ እንዳልሰረቀች ብትናገርም ተፈተሸች። ምንም አልተገኘም፡፡ በዚህ ተበሳጭታ ልጅቷን ከ3ኛ ፎቅ መኖሪያ ቤት ወርውራታለች ተብላ የተጠረጠረችው ሶፍያ መሃመድ፣ በፖሊስ ከተያዘች በኋላ ተለቃለች፡፡ ሠሚራ አብዲ ጥርሶቿ በሙሉ የረገፉ ሲሆን ጉልበቷም ተሰባብሯል፡፡
ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባት ኮማ ውስጥ የነበረችው ሰሚራ፤ ድሬዳዋ ተወስዳ በኢትዮ ጅቡቲ የምድር ባቡር የፈረንሳይ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላት ነው። በቦታው ያገኘናት ሲስተር ሂሩት እንደምትለው፤ ሰሚራ ወደ ሆስፒታል ስትመጣ እጅግ ተዳክማ ራሷን አታውቅም ነበር፡፡ ህጻኗ የመሻሻል ሁኔታ እየታየባት መሆኑን የተናገረችው ሂሩት፤ ስለ ጉዳቷ መጠንና ስለ ጤንነቷ ሁኔታ ሙሉ መረጃ መስጠት የሚችሉት ህክምና የሚያደርጉላት ዶክተሮች እንደሆኑ ጠቁማ፤ በጥቅሉ ግን ጉልበቷ መሰባበሩን እና 12 ጥርሶቿ መርገፋቸውን ገልፃለች፡፡

በተጠርጣሪነት በፖሊስ ተይዛ የተለቀቀችው ወ/ሮ ሶፍያ መሃመድ ሆስፒታሉ በመምጣት ሰው በሌለበት አሳቻ ሰዓት ገብታ ህፃኗን ለማባበልና ለማስፈራራት እንደሞከረች ሲስተር ሂሩት ገልፃ አሁን ግን ለህፃኗ ጥበቃና ክትትል እየተደረገላት ነው ብላለች፡፡ መርማሪ ፖሊስ ምክትል ሳጅን ኻሊድ አብድልፈታ የሱፍ፤ ምርመራው ሳይጠናቀቅ ተጠርጣሪዋ እንድትለቀቅ የከተማው ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቃል ትዕዛዝ እንደሰጠ ገልፀዋል፡፡ ተጎጂዋ ህፃን አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እያለችና የፖሊስ ምርመራው ሳይጠናቅቅ ተጠርጣሪዋ ከእስር መለቀቋ አግባብ አይደለም፤ በህጻኗ ደህንነት ላይም አደጋ ሊያመጣ ይችላል ብለዋል - መርማሪ ፖሊሱ፡፡
http://www.addisadmassnews.com

No comments:

Post a Comment