Wednesday, February 27, 2013

የስድስተኛው ፓትርያርክ ምርጫ ሐሙስ ይካሔዳል


•    አምስት የግብፅ ጳጳሳትም ድምፅ ይሰጣሉ
•    በዓለ ሲመቱ በኮፕቲክ ቴሌቪዥን በቀጥታ ይተላለፋል

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስድስተኛውን ፓትርያርኳን ሐሙስ የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም. በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ ውስጥ እንደምትመርጥ አስታወቀች፡፡
ለፓትርያርክነት የሚወዳደሩት አምስቱን ዕጩዎቿንም ባለፈው ሰኞ ይፋ አድርጋለች፡፡

የቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ያቋቋመው አስመራጭ ኮሚቴ ሰብሳቢ የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የካቲት 18 ቀን በመንበረ ፓትርያርክ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ለፓትርያርክነት የሚወዳደሩት አምስቱ ዕጩዎች ብፁዕ አቡነ ማትያስ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት ሊቀ ጳጳስ (ዕድሜ 71)፣ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ (ዕድሜ 75)፣ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የባሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ (ዕድሜ 61)፣ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የምዕራብና ደቡብ አዲስ አበባ፣ የከፋ ሸካ ቤንች ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ (ዕድሜ 59)፣ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የወላይታና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ (ዕድሜ 50) ናቸው፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔና የአስመራጭ ኮሚቴ አባላት በተገኙበት በተሰጠው መግለጫ፣ 2,791 ጥቆማዎች ለኮሚቴው መድረሳቸውን፣ ከእነዚህም 15ቱ ባግባቡ ባለመሞላታቸው መሰረዛቸውን አውስተው፣ ለፓትርያርክነት ከተጠቆሙት 36 ሊቃነ ጳጳሳት የመጀመርያውን ማጣሪያ 19ኙ ያለፉ ሲሆን፣ የመጨረሻዎቹ አምስቱ የተለዩት ከስምንቱ መካከል መሆኑን፣ ይህም በዕድሜና በሌሎች መስፈርቶች በተደረገ ምርጫ መሆኑን ሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡

የአስመራጭ ኮሚቴው የምርጫ ሕገ ደንቡን መሠረት አድርጎ ለዕጩ ፓትርያርክነት ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ ያቀረባቸው አምስቱ ብፁዓን አባቶች የካቲት 16 ቀን በተካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ ይሁንታ ማግኘታቸውንም አስረድተዋል፡፡

ሐሙስ የካቲት 21 ቀን በሚደረገው ምርጫ ድምፅ የሚሰጡት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የቤተ ክህነት የመምርያና የድርጅት ኃላፊዎች፣ ከ53 አህጉረ ስብከት የሚወከሉ የካህናት፣ የምዕመናንና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ የአድባራትና የገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ በውጭ አገር ከሚገኙ አህጉረ ስብከት ተወካዮች፣ የማኅበረ ቅዱሳን ተወካይ መሆናቸው ታውቋል፡፡

በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ባለው የፕሮቶኮል ስምምነት መሠረትም የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አምስት ጳጳሳትም ድምፅ ይሰጣሉ፡፡ በቅርቡ በተካሄደውና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎድሮስ ፓትርያርክ ሆነው በተመረጡበት የግብፅ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ምርጫም በተመሳሳይ ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት ድምፅ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡

የፓትርያርክ ምርጫው የወጣውን ሕገ ደንብ ተከትሎ መካሄዱን ለመታዘብ የእኅት አብያተ ክርስቲያናት የግብፅ፣ የሶርያ፣ የአርመን፣ የህንድ፣ የዓለምና የአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤቶች ተወካዮችና ሦስት የአገር ሽማግሌዎች ይታዘቡታል፡፡ ስድስተኛውን ፓትርያርክ የሚመርጡት ቁጥራቸውም 800 መሆኑን አስቀድሞ መገለጹ ይታወቃል፡፡

ስድስተኛው ፓትርያርክ ሆኖ የሚመረጠው አባት በዕለቱ ከምሽቱ 12 ሰዓት በመገናኛ ብዙኀን አማካይነት ለሕዝብ ይፋ እንደሚሆን፣ በዓለ ሲመቱም እሑድ የካቲት 24 ቀን በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም ታውቋል፡፡

ከመንበረ ፓትርያርክ የውጭ ግንኙነት መምርያ ባገኘነው መረጃ መሠረት በበዓለ ሲመቱ ላይ ከሚገኙት መካከል የህንድ ኦርቶዶክስ መንበረ ቶማስ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማርቶማ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ የግብፅ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ አቡነ ቢሾይ እና የአርመንና የሶርያ ሊቃነ ጳጳሳት ይገኙበታል፡፡

የእሑዱን በዓለ ሲመት የኮፕቲክ ቴሌቪዥን (ሲቲቪ) በቀጥታ ሥርጭት እንደሚያስተላልፈውም ታውቋል፡፡

የመጀመርያውን ፓትርያርኳን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስን በ1951 ዓ.ም. የመረጠችው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን፣ ባለፉት 53 ዓመታት አምስት ፓትርያርኮች ብፁዓን ወቅዱሳን አቡናት ባስልዮስ፣ ቴዎፍሎስ፣ ተክለ ሃይማኖት፣ መርቆሬዎስ  የመሯት ሲሆን፣ አምስተኛው ፓትርያርክ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ (1928-2004) በመንበሩ ላይ 20 ዓመት (1984-2004) ከቆዩ በኋላ ያረፉት ነሐሴ 10 ቀን 2004 ዓ.ም. እንደነበረ ይታወሳል፡፡ 
 http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment