Saturday, January 5, 2013

የበረራ አስተናጋጇን ዓይኖች ያጠፋው ግለሰብ ቅጣት ከ14 ወደ 20 ዓመታት ከፍ አለ


የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና የበረራ አስተናጋጅ የነበረችውን አበራሽ ኃይላይን ሁለት ዓይኖች በማጥፋቱ 14 ዓመታት ፅኑ እስራት ተወስኖበት የነበረው ፍርደኛው ፍስሐ ታደሰ፣ ቅጣቱ በይግባኝ ወደ 20 ዓመታት ፅኑ እስራት ከፍ አለ፡፡

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ የወንጀል ችሎት ተወስኖበት የነበረውን የ14 ዓመታት ፅኑ እስራት የቅጣት ውሳኔ በመቃወም፣ ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በየካቲት ወር 2004 ዓ.ም. ያቀረበው የይግባኝ አቤቱታ ላይ ውሳኔ የተሰጠው ታኅሳስ 26 ቀን 2005 ዓ.ም. ነው፡፡



በበረራ አስተናጋጇ ላይ ወንጀሉ የተፈጸመው መስከረም 2 ቀን 2004 ዓ.ም. ገርጂ ኮንዶሚኒየም ቤት ውስጥ ሲሆን፣ ፍርደኛው አቶ ፍስሐ ታደሰ ሁለት ዓይኖቿን በስለት ጐልጉሎ በማውጣቱ፣ በከባድ የሰው መጉደል ሙከራ፣ ከባድ የአካል ማጉደልና ሕገወጥ የጦር መሣርያ ይዞ መገኘት ወንጀል ክስ ተመሥርቶበት ነበር፡፡

ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ባቀረባቸው የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ፍርደኛው እንዲከላከል ብይን የተሰጠ ቢሆንም፣ የዓቃቤ ሕግ ማስረጃዎችን ማስተባበል ባለመቻሉ ጥፋተኛ ብሎታል፡፡

ዓቃቤ ሕግ አቅርቧቸው የነበሩት የቅጣት ማክበጃዎች ሰባት ነጥቦችን ማለትም የወንጀል አፈጻጸሙ አደገኛና ነውረኛ መሆኑን፣ ተበዳይ የቀድሞ ባለቤቷ በመሆኑ ያደረባትን እምነት ለወንጀል መፈጸሚያ ማድረጉ፣ ድርጊቱን የፈጸመው ጨለማን ተገን አድርጐ መሆኑ፣ ቋሚ የአካል ጉዳተኛ ማድረጉ፣ መደበኛ ሥራዋን እንድታጣ ማድረጉንና ተደራራቢ ወንጀሎችን መፈጸሙን በመጥቀስ ቅጣቱ ከብዶ እንዲወሰንበት ፍርድ ቤቱን ጠይቆ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ ግን የወሰደው የቅጣት ማክበጃ ጨለማን ተገን አድርጐ የሚለውን ብቻ መሆኑን ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ባቀረበው ይግባኝ ላይ ጠቅሷል፡፡

ፍርደኛው ያቀረበውን ሦስት የቅጣት ማቅለያ ሐሳቦች ማለትም ድርጊቱን ፈጽሞ ሳይሸሸግ እጁን ለፖሊስ መስጠቱን፣ ከኤችአይቪ ቫይረስ ጋር የሚኖር መሆኑንና ፍርድ ቤቱ በሕግ የተጠቀሰውን ልዩ የማቅለያ ሐሳብ እንዳለ ወስዶለት የቅጣት እርከኑ ዝቅ እንዲል አድርጐለታል፡፡

በሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ቅር ተሰኝቶ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበለትን አቤቱታ የመረመረው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለተኛ የወንጀል ችሎት በሰጠው የቅጣት ውሳኔ፣ የሥር ፍርድ ቤት የዓቃቤ ሕግን የቅጣት ማክበጃ ሐሳቦች ከአንዱ በስተቀር ሁሉንም ውድቅ ማድረጉ አግባብ አለመሆኑን ገልጿል፡፡ በመሆኑም የወንጀል አፈጻጸሙ ነውረኛና ከባድ መሆኑን፣ ተበዳይ የቀድሞ ባለቤቷ መሆኑን አይታ ያሳደረችውን እምነት ለወንጀል መፈጸሚያ ማድረጉንና ጨለማን ተገን አድርጐ ወንጀል መፈጸሙን በመውሰድ፣ የቅጣት እርከኑ ከፍ እንዲልና የቅጣት መነሻው ዕድሜ ልክና ሞት እንዲሆን አድርጓል፡፡ ነገር ግን ፍርደኛው ለሥር ፍርድ ቤት አቅርቦት የነበረውን የቅጣት ማቅለያ እንዳለ በመውሰድና የቅጣቱን እርከን ዝቅ በማድረግ ሊያርመውና ሌሎችን ሊያስተምር ይችላል ያለውን የ20 ዓመት ፅኑ እስራት በመወሰን መዝገቡን ዘግቷል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com/

No comments:

Post a Comment