Sunday, December 30, 2012

ስደተኛዋን ሉሲ ለማስመለስ እንቅስቃሴ ተጀመረ


-    በአምስት ወራት ከ244 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አገኘ
በሔኖክ ያሬድ
በኢትዮጵያ ሦስተኛው ሺሕ ዓመት (ሚሌኒየም) ዋዜማ አሜሪካ ያቀናችው ሉሲና ሌሎች ቅርሶች ወደ አገራቸው የሚመለሱበት እንቅስቃሴ መጀመሩን ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ በአምስት ወራት ውስጥም ከቱሪስቶች ከ244 ሚሊዮን ዶላር በላይ መገኘቱን ገልጿል፡፡ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሰሞኑን የአምስት ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት ሚኒስትሩ አቶ አሚን አብዱል ቃድር ለእንደራሴዎቹ እንደተናገሩት ባለፉት አራት ዓመታት በሂውስተን፣ ሲያትል እንዲሁም በተለያዩ ሙዚየሞች ለዕይታ የቀረቡት ሉሲና ሌሎች ቅርሶች ስለሚመለሱበት ሁኔታ አስፈላጊ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ይገኛል፡፡
እንደሚኒስትሩ አገላለጽ፣ የአገሪቱን በጎ ገጽታ ለመገንባትና የኢትዮ አሜሪካን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማጠናከር በ2000 ዓ.ም. የሉሲ ቅሪተ አካልን ጨምሮ 149 ቅርሶች ‹‹Lucy Legacy: The Hidden Treasures of Ethiopia›› ፕሮጀክት ከአሜሪካ የሂዩስተን የተፈጥሮ ሳይንስ ሙዚየም ጋር በተፈረሙት የአምስት ዓመታት የዓውደ ርዕይ ስምምነት ቅርሶቹ እንደሔዱ ይታወሳል፡፡ 

ኢትዮጵያን ባለፉት አምስት ወራት ከጎበኙ 272 ሺሕ 541 ቱሪስቶች 244 ሚሊዮን 196 ሺሕ 736 ዶላር ገቢ መገኘቱና ይህም ከታቀደው የገቢ መጠን 62 በመቶ መሳካቱን የሚኒስቴሩ ሪፖርት አመልክቷል፡፡ ገቢው ቱሪስቶች በአገር ውስጥ ቆይታቸው የሚያወጡትን የተለያዩ ወጪዎች በማካተት የተገኘ ነው፡፡ በተጠቀሱት ወራት ውስጥ ለ308 ሺሕ የውጭ ቱሪስቶች አገሪቱን በማስጎብኘት 396 ሚሊዮን ዶላር ለማስገባት አቅዶ እንደነበረም ተናግሯል፡፡ 
በሌላ በኩል ሚኒስቴሩ በፋሺስት ኢጣሊያ ተዘርፎ ሮም ተወስዶ የነበረውን የአክሱም ሐውልት ለማስመለስ በተደረገው ጥረት የተሳተፈው የአክሱም ሐውልት አስመላሽ ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴን በክብር ለማሰናበት መወሰኑን አስታውቋል፡፡ ኮሚቴው ከ1990 እስከ 2001 ዓ.ም. ሐውልቱን ለማስመለስ ባደረገው የሥራ እንቅስቃሴ በኮሚቴው የገቢና የወጪ ሒሳቦች በዋናው ኦዲተር ምርመራ ተደርጎ በኅዳር 2005 ዓ.ም. በኦዲት ሪፖርቱ በተገለጹት አምስት ግኝቶች ላይ የመውጫ ስብሰባ ከብሔራዊ ኮሚቴ አባላት ጋር ተደርጎ ሪፖርቱ ተጠናቅቆ መግባባት ላይ መደረሱን፣ ለሒደቱ ማጠቃለያነትም የብሔራዊ ኮሚቴውን ክንውን ለታሪክ የሚሆን የማጠቃለያ ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማቅረብ ስንብት ለማከናወን መወሰኑን ገልጿል፡፡
በቀጣዩ አንድ ወር ውስጥም የማጠቃለያ ሪፖርቱ ተዘጋጅቶ የኮሚቴ አባላትና ለሒደቱ አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላት ከአክሱም ሕዝብ ጋር የምስጋና ፕሮግራም በሚዘጋጅበት አግባብ ላይ ለመሥራት ውሳኔ መተላለፉን ሚኒስትሩ አመልክተዋል፡፡
የአገሪቱ የቋንቋ ፖሊሲ የመጨረሻው ረቂቅ እንዲሁም የባህል ፖሊሲ መከለሱን፣ ከክልሎችና ከባለድርሻ አካላትና ከሚመለከታቸው ጋር ሰፊ ውይይት በማድረግ በአራተኛው ሩብ ዓመት ለማጠናቀቅ መታቀዱንም ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
ለብሔራዊ ፓርኮች፣ ጥበቃ ቦታዎችና ለቅርስ ጥበቃ ተብሎ የሚመደብ የሎጂስቲክ ድጋፍ እጅግ አነስተኛ መሆን፣ በጥበቃ ቦታዎች በብሔራዊ ፓርኮች ውስጥ ሕገወጥ ወረራ፣ ሕገወጥ አደንና የእርሻ መስፋፋት ካጋጠሙት ችግሮች ውስጥ እንደሚገኙበት ያመለከተው ሚኒስቴሩ ተግዳሮቶቹን ለመቅረፍ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ፓርላማው ድጋፍ እንዲያደርግለት ተማጽኗል፡፡
3.2 ሚሊዮን ዓመታት ያስቆጠረችውና በሳይንሳዊ ስሟ ‹‹አውስትራሎፒቲከስ አፋራንሲስ›› በመባል የምትታወቀው ሉሲ (ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ስሟ ድንቅነሽ)፣ በአፋር ሐዳር ውስጥ በ1966 ዓ.ም. የተገኘችው በአሜሪካዊው ፓሊዎአንትሮፖሎጂስት ዶናልድ ጆንሰን መሆኑ ይታወቃል፡፡ ቅሬተ አካሏ የተሟላ አካል ያለው መሆኑ የተነገረላት ሉሲ ስሟን ከአንድ ዘፈን ማግኘቷ ይታወሳል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment