Sunday, December 30, 2012

ሞት ማለት እና መክሸፍ ፦ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም


ሞት ማለት፦
ሞት ማለት
ተንጋሎ መተኛት፤አለመንቀሳቀስ
ፍፁም የእንቅልፍ አለም፤ፍፁም የህይወት ቀውስ፤
አለመደሰት ነው፤ተከፍቶ አለማልቀስ፤
የሬሳ እኩልነት፤ርኩስ የለቅዱስ፤
በኅብረት መበስበስ፤በየቀኑ መፍረስ
ሞት አለመስማት፤ነው ጆሮ ዳባልበስ፤
ክርስቶስ ሲሰቀል፤ሲፈታ ባርናባስ፡፡
ሞት ማለት፦
አለመናገር ነው ጭው ያለ ዝምታ፤
የመቃብር ሰላም የሬሳ ፀጥታ፤
ደሀ በሰሌኑ ሳጥን ገብቶ ጌታ፤
የውሸት ልዩነት ተጋድሞ በተርታ፤
አይመሽ ወይ አይነጋ፤ጠዋት የለ ማታ፡፡
ሐዘን የለ ለቅሶ፤ደስታ፤ፈገግታ፤
ዘፈኑና ለቅሶው የምስጥ ሹክሹክታ፡፡
ሞት ማለት፦
አይረገዝበት፤አይወለድበት፤
የመቃብር አለም፤ጭንጋፍ፤የጭንጋፍ ቤት፤
የሰው ልጅ እንደበት ትል የሚሆንበት፤
ክርክር የለበት፤ውድድር የለበት፤
ውሸትና እውነት በማይበርድ ፍትወት የተሳሰሩበት
የድብቅብቅ አለም ምስጢር የበዛበት፤
ሁሉም በየጉድጓዱ የተሸሸገበት፡፡
ሞት ማለት፦
አለመነቃነቅ፤አለመነቃነቅ፤
እንደድንጋይ መድረቅ፤ደርቆ መወላለቅ፤
ክብርና ውርደትን ለይቶ አለማወቅ፤
አዘቅት ውስጥ ተኝቶ በክፋት ነጥለቅለቅ፤
በተዋኅዶ መልክ ጠላትና ወዳጅ አብሮ ሲደባለቅ
ድፍርሱ ከጠራው ባህርዩ ሲደበቅ
የሩቁ ሲጠጋ የቅርቡ ሲራራቅ፤
ሞት አምሮት ሲጠፋ በልጦ ለመመረቅ፡፡
ሞት ማለት፦
ሞት አለመስጋት ነው የግዴለሽ አለም፤
ድንጋይ ተሸክሞ በውሃ ላይ መቆም፤
ጤንነት የለበት፤አያጠቃው ሕመም፤
ትዝታ የለበት፤አይታይበት ሕልም፤
ቡቃያው አያሸት፤ ፍሬው አይለመልም፡፡
ዝናብ አይዘንብበት ድርቀት ነው ዘላለም፡፡
ሞት ማለት፦ የሞት ሞት
አዕምሮ ፈራርሶ፤
ኅሊና በስብሶ፤
ሰውነት ረክሶ፤
እንደግም፤እንደጥንብ፤
የጭልፊቶች ምግብ፤
የሞት ሞት ይኸ ነው፤
ትንሳኤ የሌለው፡፡
መስፍን ወልደማርያም
እንጉርጉሮ
1967 ዓ.ም.
..............................................................................................................
መክሸፍ መከሻሸፍ በርትቶ ስራ መስራት፤ዘለቄታ ያለው ስራ መስራትና ለሕዝቡ እውቀትንና ብልፅግናን፤ለአገሪቱ ኃይል ማስገኘት አልተቻለም፡፡ለምን? የአክሱምን ሃውልት የላሊበላን ከድንጋይ የተፈለፈሉ ቤተክርስቲያኖች፤የጎንደር ቤተ መንግስቶች የሰራ ሕዝብ ከደሳሳ ጎጆ ጋር ተቆራኝቶ ለብዙ ምዕተ-ዓመታት የቆየበት ምክንያት ምንድን ነው? ይህ ጥያቄ የታሪክ ሊቃውንቱንና ተመራማሪዎቹን እንዴት ሳይኮረኩራቸው ቀረ? ይህንና ሌሎች ብዙ የመክሸፍ እንቆቅልሾች እንዴት ሳያዩ ቀሩ?ወይስ እንዴት ችላ ብለው አለፏቸው?
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ 

No comments:

Post a Comment