Wednesday, July 18, 2012

የሃይሌ ገብረስላሴ ግዝት በሸካ ሽማግሌዎች


ዝነኛው አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በግብርና ሚኒስቴር አማካይነት በሊዝ የተፈቀደለትን 1,500 ሔክታር መሬት ለመረከብ በደቡብ ክልል ሸካ ዞን በተገኘበት ወቅት፣ የአካባቢው ሽማግሌዎች በመሬቱ ላይ ያለውን ደን እንዳይጨፈጭፍ ገዘቱት፡፡

ኃይሌ የተሰጠው መሬት በክልሉ ዋና ከተማ ከሐዋሳ ከተማ 951 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሸካ ዞን ማሻ ወረዳ የጶ ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡ መሬቱ ሙሉ ለሙሉ ጥቅጥቅ ያለ የተፈጥሮ ደን ያለበት ሲሆን፣ የአካባቢው ሽማግሌዎች አትሌቱ ደኑን እንዳይጨፈጭፍ ገዝተውታል፡፡

ኃይሌ ይህንን መሬት በሔክታር 63 ብር ሒሳብ ለ45 ዓመት የሊዝ ዘመን ተረክቧል፡፡ አካባቢው መንገድ የሌለው በመሆኑ ኃይሌ 14 ኪሎ ሜትር መንገድ መገንባት ይጠበቅበታል፡፡ ‹‹ከመንገዱ በተጨማሪ ሁለት ወንዞች ስላሉ ድልድይም እገነባለሁ›› ሲል ኃይሌ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ ኃይሌ ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ የቡና፣ የቅመማ ቅመም ልማቱና የመንገድ ግንባታው ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ይፈልጋል፡፡

በአካባቢው ውብ ተፈጥሮ እጅግ መደሰቱን ለሪፖርተር የገለጸው ኃይሌ፣ ደኑን እንዳይቆርጥ የአካባቢው ሽማግሌዎች እንደገዘቱት አስረድቷል፡፡ ቡና በተፈጥሮው የዛፍ ጥላ ስለሚወድ ደኑን እንደማይጨፈጭፍ ኃይሌ አስታውቆ፣ የአካባቢው ሕዝብ ፍላጎት ከሆነ ቦታውን በይዞታው ሥር በማድረግ እንዲሁ ሊዝ እየከፈለ እንደሚያቆየው አስረድቷል፡፡

በሕንፃ ግንባታ፣ በሆቴል፣ በአውቶሞቢል አስመጪነትና በተለያዩ የንግድ ሥራዎች የተሰማራው  አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ በእርሻ ሥራ የመሰማራት ህልም እንዳለው ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ ይህንን ዕቅዱን ለማሳካት ለደቡብ ክልል መንግሥት ከዓመታት በፊት የቦታ ጥያቄ ቢያቀርብም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ተፈጻሚ ሳይሆን ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን የግብርና ሚኒስቴር 1,500 ሔክታር መሬት እንዲሰጠው በመወሰኑ ቦታውን የደቡብ ክልል መንግሥት አስረክቦታል፡፡

ወደ ውጭ የሚላኩ የግብርና ምርቶችን ማልማት ህልሙ እንደሆነ የተናገረው ኃይሌ፣ በቀጣይነት ሙሉ ትኩረቱን በእርሻ ልማት ላይ እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡ በሸካ ዞን ጥቅጥቅ ደን ውስጥ መሬት መመራቱን በጥርጣሬ የሚመለከቱ አልጠፉም፡፡

ለሪፖርተር ሥጋታቸውን የሚገልጹት የአካባቢ ተቆርቋዎች እንደሚሉት፣ የሸካ ደን ጥቅጥቅና በውስጡ ብዙ ዓይነት ዕፅዋቶች ያሉት ነው፡፡ በዚህ አካባቢ የሚገኘው የደን ሀብት መነካት እንደሌለበት በአፅንኦት በመናገር ለአትሌቱ መሬቱ ሊሰጠው እንደማይገባ ይናገራሉ፡፡

የሸካ ነዋሪዎች ለዘመናት ደን ሲንከባከቡ የኖሩ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ማኅበረሰቡ ከደን ሀብቱ ማርና ቅመማ ቅመም በማምረት የሚተዳደር ሲሆን፣ ነዋሪዎች ለሕመማቸው ፈውስ የሚያገኙት በደን ውስጥ ካሉ ልዩ ልዩ ዕፅዋት ነው፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ኃይሌ ደኑን ሳይነካ ልማቱን ቢያካሂድ እንደማይቃወሙ ታውቋል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment