Monday, April 2, 2012

አበራሽ ኃይላይ ላይ ለደረሰው ጉዳት 10.8 ሚ. ብር የጉዳት ካሣ ተጠየቀ


በኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ የበረራ አስተናጋጅ በነበረችው ሆስተስ አበራሽ ኃይላይ ላይ ጉዳት በማድረስ ሁለቱም አይኖቿ እንዲጠፋ አድርጓል በሚል ወንጀል ተከስሶ የ14 ዓመት ጽኑ እስራት በተፈረደበት የቀድሞ ባለቤቷ ላይ የ10.8 ሚሊዬን ብር የጉዳት ካሣ ክስ ቀረበበት፡፡ ክሱ የኢትዮጵያን የጉዳት ካሣ ክፍያ ህግና ሥርዓት ያልተከተለ በአገሪቱ ፈጽሞ ታይቶ የማይታወቅ ነው ሲሉ የተከሳሽ ወገኖች ተቃውመውታል፡፡

በከሳሽ ሆስተስ አበራሽ ሃይላይ እና በተከሳሽ አቶ ፍሰሃ ታደሰ መካከል በፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ሰባተኛ ፍትሃብሔር ችሎት የቀረበው ክስ እንደሚያመለክተው፤  ተከሳሹ “ጭካኔ፣ ነውረኛና አደገኛ በሆነ ሁኔታ መስከረም 2/2004 በሽጉጥ በማስፈራራትና በሰደፍ በመደብደብ የከሳሽን ሁለት ዓይን ደጋግሞ በመውጋትና ጐልጉሎ በማውጣት ከባድ የመግደል ሙከራ ፈጽሞባታል፡፡ በዚህ በተፈፀመባት ወንጀል ምክንያትም ከሳሽ እስከ ዕድሜ ልኳ ድረስ የዓይንዋን ብርሃን አጥታለች፡፡

ስለዚህም ተከሳሽ ከዚህ በኋላ ለ34 ዓመታት በህይወት ትቆያለች ተብሎ ቢታሰብ፣ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ጉዳት ሳይደርስባት ቀርቶ ቢሆን ኖሮ ሠርታ ታገኝ የነበረውን ገንዘብና በደረሰባት ጉዳት ምክንያት እንድታወጣ የምትገደዳቸውን አዳዲስ ወጪዎች ጨምሮ በአጠቃላይ ብር 10.849.739.80 ሣንቲም የጉዳት ካሣ እንዲከፍል ተጠይቋል፡፡

ተከሳሽ በከሳሿ ላይ ባደረሰው ጉዳት መሰረት፣ የጉዳት ካሣ የመክፈል የፍትሃብሔር ሃላፊነት እንዳለበት ያመለከተው የከሳሽ የክስ ቻርጅ፤ “ከሳሽ የአይን ብርሃንዋን በማጣቷ ምክንያት ከአይነስውራን ህይወት ጋር ራሷን ለማላመድና አዳዲስ ትምህርቶችን ለመማር የሚያስችላትን ወጪ ሁሉ ተከሳሽ የመክፈል ሃላፊነት አለባቸው” ይላል፡፡
በከሳሽ የቀረበውን የ10.8 ሚሊዬን ብር የጉዳት ካሣ ክፍያ ጥያቄ አስመልክቶ የተከሳሽ ዘመድ መሆናቸውን በመግለጽ አስተያየት የሰጡን አቶ ኤልያስ፤ የቀረበው የጉዳት ካሣ  ጥያቄ ክስ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ታሪክ ተሰምቶ የማያውቅና ትክክለኛ አግባብና ሥርዓት የሌለው ነው ብለዋል፡፡

አንድ ሰው ወንጀል ፈጽሞ በህግ ቁጥጥር ሥር ቢሆንም የራሱ ህጋዊ መብቶች ያሉት በመሆኑ ይህንን መብት ሊነፈግ አይገባም ያሉት አቶ ኤልያስ፤ ተከሳሹ ወንጀል ፈጽሟል ተብሎ እንደ እንስሳ ልናገልለውና አናት አናቱን ልንለው አይገባም፡፡ እሱ በህግ ጥላ ስር ቢሆንም የሚረዳቸው ደካማ እናት ያሉት በመሆኑ፣ ፍትህ ሁሉንም ወገን እኩል ሊመለከት ይገባዋል ብለዋል፡፡

በዚህ ክስ ላይ የተከሳሹን ምላሽ ለመቀበል ለመጋቢት 21/2004 ዓ.ም ቀጠሮ ተይዟል፡፡

No comments:

Post a Comment