Tuesday, January 31, 2012

ለስካይ ባስ አደጋ የሚከፈለው የጉዳት ካሳ አራት ሚሊዮን ብር ተገመተ

(ፎቶ ከ አንተነህ ይግዛው)

በቅርቡ ከአዲስ አበባ ወደ ጎንደር ሲጓዝ በነበረው የስካይ ባስ አክሲዮን ማኅበር አውቶቡስ ላይ በደረሰው አደጋ፣ የሦስተኛ ወገን አስገዳጅ የመድን ሽፋን ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ ሕይወታቸው ላለፈውና ለተጎጂዎች የሚከፍለው ትልቁ የጉዳት ካሳ እንደሚሆን ታወቀ፡፡ ለደረሰው አጠቃላይ የጉዳት ካሳ ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚከፈል ተገምቷል፡፡

ከስካይ ባስ ኩባንያ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በአደጋው ሕይወታቸው ላለፉ ቤተሰቦችና ጉዳት ለደረሰባቸው ተሳፋሪዎች ካሳ ለመክፈል ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው፡፡

ለተሽከርካሪውም ሆነ ለተሳፋሪዎቹ የመድን ሽፋን የተገባው ከመንግሥታዊ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም ስካይ ባስ ለኢንሹራንስ ድርጅቱ ስለአደጋው ሁኔታ የሚገልጽና የተጎጂዎቹን ስም ዝርዝር የያዘ መረጃ ማቅረቡ ታውቋል፡፡

በዚሁ መሠረት ኢንሹራንስ ድርጅቱ ከፖሊስ ማረጋገጫ የጠየቀ በመሆኑ፣ ለአደጋውና ለሟቾቹም የሞት አደጋ ሠርተፊኬት ለመስጠት እንዲቻል፣ የተጎጂ ቤተሰቦችን ቃል እንዲቀበሉላቸው ፖሊሶችን ወደ አዲስ አበባ በማስመጣት በስካይ ባስ ጽሕፈት ቤት እያነጋገሯቸው ይገኛሉ፡፡

በተገኘው መረጃ መሠረት ለሟቾች ካሳ እንዲከፈል ማሟላት ያለባቸው መስፈርቶች እንዳለ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡ ተሳፋሪዎች ወራሾች ከፍርድ ቤት ወራሽነታቸውን የሚያረጋግጥ መረጃ ይዘው መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡

አጠቃላይ ለደረሰው የሞትና የመቁሰል አደጋ፣ እንዲሁም ለተሽከርካሪው የሚከፈለው ካሳ ምን ያህል ነው የሚለው ጉዳይ ስካይ ባስ ኩባንያ ባይገልጽም፣ በአዲሱ የሦስተኛ ወገን አስገዳጅ የመድን ሽፋን አዋጅ መሠረት ለሟች ወራሾች ለእያንዳንዳቸው 40 ሺሕ ብር እንደሚከፈል ይደነግጋል፡፡ በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡት 42 ሰዎች የሚከፈለው ደግሞ ወደ 1.7 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ይሆናል፡፡

ከአደጋው ለተረፉትና ለተጎዱት ደግሞ እያንዳንዳቸው 10 ሺሕ ብር በላይ የሚከፈል ሲሆን፣ ለተሽከርካሪው የተገባው ዋስትናና ለሕክምና የወጣው ወጪ ሲደማመር፣ የኢንሹራንስ ኩባንያው አጠቃላይ የካሳ ክፍያው ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን ተገምቷል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለተጎጂዎቹ ጥር 27 ቀን 2004 .. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በተገኙበት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ፍትሀትና የፀሎት ሥነ ሥርዓት ይደረጋል፡፡ የፊታችን ዓርብ ደግሞ በአንዋር መስጊድም ተመሳሳይ ፕሮግራም ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ጥር 9 ቀን 2004 .. ከአዲስ አበባ 46 ተሳፋሪዎችንና ሦስት ሠራተኞችን ይዞ ወደ ጎንደር ሲያመራ ዓባይ በረሃ ህዳሴ ድልድይ መዳረሻ ሊደርስ ሲል አደጋ የደረሰበት፣ ንብረትነቱ የስካይ ባስ ኩባንያ አውቶቡስ ተገልብጦ 42 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል፡፡ በግምት 80 ሜትር በላይ ጥልቀት ያለው ገደል ውስጥ የተገለበጠው አውቶቡስ በእሳት በመያያዙ ጭምር ሰለባ የሆኑት 42 መንገደኞች አስከሬን ደጀን ከተማ መቀበሩ አይዘነጋም፡፡ ስካይ ባስ ኩባንያ ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ ለሟቾቹ መታሰቢያ አደጋው በደረሰበት ሥፍራ አንድ ትምህርት ቤት ለመሥራት አቅዷል፡፡

No comments:

Post a Comment