Wednesday, January 25, 2012

በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በተከሰሱት እነ አንዱዓለም አራጌ ላይ ብይን ተሰጠ


በግንቦት 7 አሸባሪ ድርጅት ውስጥ አመራርና አባል በመሆን የአገሪቱን ፖለቲካ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሕገ መንግሥታዊ ተቋማትን በኃይል ለማናጋት ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል በሚል ተጠርጥረው በሽብር ወንጀል ክስ የተመሠረተባቸው፣ አንዱዓለም አራጌን ጨምሮ ስምንት በአገር ውስጥ ሆነው ክሳቸውን በመከታተል ላይ ያሉና በሌሉበት ክሳቸው በመታየት ላይ የሚገኙ ተከሳሾች፣ ተጠርጥረው የተከሰሱበትን የሽብር ወንጀል እንዲከላከሉ ትናንትና ብይን ተሰጠ፡፡ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የመሠረታቸውን ስድስት ክሶችና ያቀረባቸውን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን መርምሮ ሦስተኛና አምስተኛ ክሶችን ውድቅ በማድረግ፣ ተጠርጣሪዎቹ እንዲከላከሉ ብይን የሰጠው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ነው፡፡

ፍርድ ቤቱ በቀረበባቸው ክስ እንዲከላከሉ ብይን የሰጠባቸውና በአገር ውስጥ ሆነው ጉዳያቸውን በመከታተል ላይ ያሉት አንዱዓለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንን፣ ዮሐንስ ተረፈ፣ የሸዋስ ይሁንዓለም፣ ክንፈ ሚካኤል አበበ፣ ምትኩ ዳምጤ፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና አንዱዓለም አያሌው ናቸው፡፡

ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ በአንደኛ ክስ ማለትም በግንቦት 7 አሸባሪ ድርጅት ውስጥ በአመራርነትና በአባልነት፣ በሁለተኛው ክስ የሽብርተኝነት ድርጊቶችን ለማስፈጸምና ለመፈጸም፣ በህቡዕ በሽብርተኝነት ድርጅት ውስጥ በአመራርነትና ውሳኔ ሰጭነት፣ በአራተኛ ክስ ከኤርትራ መንግሥት ጋር በህቡዕ በመገናኘት አጀንዳውን ለማስፈጸም ሚስጥራዊ ግንኙነት በማድረግ፣ አባላትን በመመልመልና ወደ ኤርትራ በመላክ በፈጸሙት የክህደት ወንጀልና በስድስተኛ ክስ የሙያ ድጋፋቸውን በመስጠታቸው በፈጸሙት የወንጀል ክሶች እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎቹ የመከላከያ ምስክሮቻቸውን ስም ዝርዝር፣ የሰነድ ማስረጃዎቻቸውን በጽሕፈት ቤት በኩል እንዲያስገቡ ትዕዛዝ ሰጥቶ መከላከያ ምስክሮችን ለመስማት ለየካቲት 26 እና 27 ቀን 2004 .. ተለዋጭ ቀጠሮ ከሰጠ በኋላ፣ አንዱዓለም አራጌና ክንፈ ሚካኤል አበበ ያላቸውን አቤቱታ ለፍርድ ቤቱ አሰምተዋል፡፡

አንዱዓለም አራጌ ባሰማው አቤቱታ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ሳለ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩና የመንግሥት መገናኛ ብዙኅን ፍርድ እየሰጡባቸው መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ቢያመለክቱም፣ ፍርድ ቤቱ አቤቱታውን ውድቅ በማድረጉ፣ አሁንም ድርጊቱ መቀጠሉን በአቤቱታ ተናግሯል፡፡ በመሆኑም የፍርድ ቤቱ ሥልጣን እየተጣሰ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለፍትሕ በእውነት የሚሠራ ከሆነ ዕርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ለአንዱዓለም አራጌ በሰጠው ምላሽ ብዙ ጊዜ ፍርድ ቤቱን እየደፈረ መሆኑን ጠቅሶ፣ ‹‹ይኼ ድርጊትህ ሊያስቀጣህ ስለሚችል ብትጠነቀቅ ጥሩ ነው፤ ፍርድ ቤቱ በቀረበለት ማስረጃ መሠረት ሕግን የመተርጐም ሥራ እየሠራ ነው፤›› በማለት አስጠንቅቆታል፡፡

ክንፈ ሚካኤል አበበ በበኩሉ ባቀረበው አቤቱታ፣ ተመሥርቶበት በነበረው አምስተኛ ክስ የኤርትራና የአሸባሪዎች ተላላኪ ሆኖ ይሠራ እንደነበር ቢሆንም፣ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበበት ማስረጃ ባለመኖሩ ፍርድ ቤቱ ክሱን ውድቅ እንዳደረገው በማስታወስ፣ አሁንም ግን ከኤርትራ መሪዎች ጋር እያሳየው መሆኑን በመጥቀስ፣ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት እንዲጠየቅለት አመልክቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ ግን አቤቱታውን ውድቅ አድርጐታል፡፡

No comments:

Post a Comment