Wednesday, December 14, 2011

የሆስተሷ የቀድሞ ባለቤት መከላከያ ምስክሮቹን አሰምቶ ጨረሰ


‹‹ጥፋተኛ ነው አይደለም›› በሚለው ላይ ፍርድ ለመስጠት ተቀጥሯል

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በመሠረተበት ከባድ የአካል ማጉደል፣ የግድያ ሙከራና በሕግ የተከለከለ ሕገወጥ መሣርያ ይዞ መገኘት የወንጀል ክሶች፣ የመከላከያ ምስክሮቹን ሊያሰማ የነበረው የሆስተስ አበራሽ ኃይላይ የቀድሞ ባለቤት አቶ ፍስሐ ታደሰ፣ የመከላከያ ምስክሮቹን ለፍርድ ቤት ህዳር 27 ቀን 2004 .. አሰምቶ ጨረሰ፡፡ ተከሳሹ ክሱን በመመርመር ላይ ለሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ህዳር 27 ቀን 2004 .. ከሆስተስ አበራሽ ጋር ከተለያየ በኋላ፣ በአዕምሮው ላይ ተከስቶበት የነበረውን ችግር የሚያስረዱለት፣ አንድ የሙያ መከላከያ ምስክር አቅርቦ እንደሚያሰማ ቢያሳውቅም፣ የሙያ ምስክሩ በችሎት ቀርበው ለመመስከር ፈቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው እንደተዋቸው አስታውቋል፡፡

አቶ ፍስሐ ከሆስተስ አበራሽ ጋር ያደረጋቸውን የስልክ ንግግሮችንና የሐኪም ቤት የሕክምና ማስረጃ የሰነድ ማስረጃዎች ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል፡፡

የተከሳሹ ጠበቆችና ዓቃቤ ሕግ፣ የየራሳቸውን የሰው ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃዎች ለፍርድ ቤቱ አሰምተውና አቅርበው በመጨረሳቸው፣ የክርክር ማቆሚያ ሐሳባቸውን ከቀጠሮ በፊት በጽሕፈት ቤት በኩል እንዲያስገቡ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሲሰጥ፣ የተከሳሽ ጠበቆች ‹‹ክቡር ፍርድ ቤት የምናመለክተው አለን›› አሉ፡፡

ጠበቆቹ ሁለት ጋዜጦችን በእጃቸው ይዘው የሚያመለክቱት ነገር እንዳላቸው ሲጠይቁ፣ ከክሱ ጋር የተያያዘና ለፍርድ አሰጣጥ በጣም የሚጠቅም ካልሆነ በስተቀር አቤቱታቸውን በጽሕፈት ቤት በኩል እንዲያቀርቡ ፍርድ ቤቱ ጠየቀ፡፡ ጠበቆቹ የተለየና የሚጠቅማቸው መሆኑን ቢናገሩም፣ ፍርድ ቤቱ ተደራራቢና ብዙ ሥራ እንዳለበት በመግለጽ ያላቸውን ቅሬታ በሙሉ በጽሕፈት ቤት በኩል እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሊሰጥ ሲል፣ ተከሳሹ ‹‹እንደወጣሁ ነው የቀረሁት፣ ስለ ንብረቴ ነገር ቀደም ብዬ ባመለክትም መልስ አላገኘሁም›› በማለት አመለከተ፡፡ የችሎቱ ዳኞች እርስ በእርሳቸው ከተመካከሩ በኋላ ከጠበቆቹ ጋር ተነጋግረው በጽሕፈት ቤት በኩል እንዲያቀርብና ትዕዛዝ እንደሚሰጡበት ከነገሩት በኋላ፣ በተከሰሰበት ወንጀል ‹‹ጥፋተኛ ነው ወይስ አይደለም›› በሚለው ላይ ፍርድ ለመስጠት ለታህሳስ 11 ቀን 2004 .. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥተዋል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment