Saturday, December 10, 2011

አሸባሪዎችን ጨምሮ ማንንም ማነጋገር እንደሚቻል የስዊድናዊያኑ ጋዜጠኞች ምስክር ተናገሩ


የጋዜጠኝነት ሙያቸውን ከለላ በማድረግ፣ የኦብነግን የሽብር ዓላማ በመደገፍ፣ በሕገወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው የሽብር ወንጀል ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ሥር ውለዋል በሚል፣ ክስ የተመሠረተባቸው ሁለት የስዊድን ጋዜጠኞች የመከከላከያ ምስክር፣ በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ አሻባሪዎችን ጨምሮ ከማንም ጋር ቃለ መጠይቅ ማድረግ እንደሚቻል ህዳር 27 ቀን 2004 .. ለፍርድ ቤት ተናገሩ፡፡ የተከሳሾቹ ሦስተኛና የሙያ መከላከያ ምስክር ሆነው የቀረቡት ስዊድናዊው ሚስተር ማቲያስ ዮራንሰን፣ ክሱን እየመረመረው ለሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ስለጋዜጠኝነት ሙያ የተናገሩት፣ የተከላካይ ጠበቃ ደርበው ተመስገን ‹‹በዓለም የዜና ማሰራጫ ስንመለከት ጋዜጠኞች ከአሻባሪዎች፣ ከታጣቂዎች፣ ከፖለቲከኞችና ከመንግሥታት ጋር ሲነጋገሩ ይታያሉ፤ እስቲ ስለ እናንተ አሠራር ግለጹልን፤›› የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡላቸው ነው፡፡

ምስክሩ ጨምረው እንዳስረዱት፣ ቺቺኒያን ለማስገንጠል ከሩሲያ መንግሥት ጋር የሚዋጉትን አማፂያንን በሚመለከት የሩሲያን ጦር ለማግኘት ወደ ሥፍራው በሕጋዊ መንገድ መጓዛቸውን ተናግረው፣ በዚያው አማፂያኑን ለማነጋገር በሕገወጥ መንገድ መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ መንገድ የሒዝቦላህን፣ የሐማስን፣ የኮንጎ አማፅያንንና ሌሎቹንም ማነጋገራቸውን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡

ተከሳሾቹ ጋዜጠኛ ማርቲንና ፎቶ ጋዜጠኛ ጁሃን የዘገቡትን በጋዜጦች ላይ ማንበባቸውና ወደ እንግሊዘኛ ተተርጉሞ ማየታቸውን የገለጹት ሚስተር ዮራንሰን፣ ሙያውን የጠበቀና ሁሉም የምዕራብ አገር ጋዜጠኞች የሚያሟሉትን የአጻጻፍ ዘዴና እውነታን የተከተለከ ዘገባ መሆኑን መስክረዋል፡፡

ዜግነታቸው ስዊድናዊ ቢሆንም የሚኖሩት በእስራኤል አገር እየሩሳሌም ውስጥ መሆኑን የገለጹት የመከላከያ ምስክሩ፣ 12 ዓመታት በላይ በጋዜጠኝነት መሥራታቸውንና እየሠሩ መሆኑን፣ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በታሪክ ካገኙ በኋላ ወደ ኬንያ በመሄድ ለሁለት ዓመታት ተጨማሪ የጋዜጠኝነት ሥልጠናዎችን መውሰዳቸውን፣ ናይሮቢና ባግዳድ ሆነው ለዘኢኮኖሚስት፣ ለሮይተርስ፣ ለኢየሩሳሌም ፖስትና ለሌሎቹም መገናኛ ብዙኃን የሙያውን ሥነ ምግባር የጠበቀ ዘገባ መሥራታቸውን አስታውቀዋል፡፡

በመካከለኛው ምሥራቅና በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ለሥራ መንቀሳቀስ ካስፈለገ ጠባቂዎችን መቅጠር የግድ መሆኑን የገለጹት ሚስተር ዮራንሰን፣ አንዳንድ ጊዜ የመታገት፣ የመገደልና የቦምብ ሰላባ መሆን  እንደሚያጋጥም አውስተው፣ ከኢዝቦላህ ጋር ሆነው ሲሠሩ በእስራኤል ወታደሮች ታግተው እንደነበርና ወደ ሚሠሩበት ሚዲያ ተደውሎ በሰዓታት ውስጥ እንደተላቀቁ ምሳሌ በመጥቀስ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

ጋዜጠኛ ማርቲን ካርል ሽብዬና ፎቶ ጋዜጠኛ ጁሃን ካርል ፐርሰን ከስዊድን ወደ እንግሊዝ፣ ከእንግሊዝ ወደ ኬንያ፣ ከኬንያ ወደ ሶማሊያ ከዛም ያለምንም ሕጋዊ ፈቃድ በሕገወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ከአሸባሪው ኦብነግ ጋር ሆነው ሲንቀሳቀሱ፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ ልዩ የፖሊስ ኃይል ከኦብነግ ታጣቂዎች ጋር  ባደረገው ውጊያ ወቅት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንና በሽብር ወንጀል መከሰሳቸውን አስመልክቶ፣ ጋዜጠኞቹ የፈጸሙት ድርጊት ከጋዜጠኛ የሥነ ምግባር መርሆዎች አንጻር ‹‹ትክክል ነው ወይስ ትክክል አይደለም?›› የሚለውን ለማሳየት ሦስተኛ የመከላከያ ምስክር ሆኖ የቀረቡት ሚስተር ዮራንሰን፣ ከራሳቸው ልምድ በመነሳት የሙያ ምስክርነታቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

በጋዜጠኝነት ሙያ ተሰማርቶ በአሜሪካ ድምፅ፣ በካናዳ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን፣ በፎክስ ኒውስና በሌሎች በርካታ የመገናኛ ብዙኃን ውስጥ 20 ዓመታት በላይ እንደሠሩና እየሠሩ እንደሚገኙ የገለጹት አሜሪካዊው ሚስተር ፊሊፕ ኢትሆድ፣ ለጋዜጠኛ ማርቲንና ለፎቶ ጋዜጠኛ ጁሃን አራተኛው የሙያ መከላከያ ምስክር ሆኖ በመቅረብ፣ ስለ ጋዜጠኝነት ሙያ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

ካሊፎርኒያ ውስጥ በብሮድካስት ጆርናሊዝም ከተመረቁ በኋላ በሥራው ውስጥ እንደሚገኙ የተናገሩት የመከላከያ ምስክሩ፣ ‹‹ዋናውና ተቀዳሚው የጋዜጠኛ ሥራ ወገንተኝነት የሌለበት መረጃ ለሕዝብ ማቅረብ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ግጭት በበዛባቸው አገሮችና ቦታዎች ላይ ተገኝቶ ለመዘገብ፣ አንዳንድ ጊዜ በግልጽ፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በሚስጥር፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ወይም ከአገር ውስጥ በተቀጠሩ ጠባቂዎች ታጅቦ እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡

በአሸባሪነት የተፈረጁ ተቋማት ኃላፊዎችን አነጋግረው እንደማያውቅና ትክክለኛ መረጃን ለማግኘት በሕገወጥም ሆነ በሕጋዊ መንገድ አገሮችን አቋርጦ በመግባት መሥራት፣ የሥራው ባህሪ መሆኑን በመናገር የመከላከያ ምስክርነት ቃላቸውን አጠቃለዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በመከላከያ ማስረጃነት የቀረበውንና አስተርጓሚዎችን ጭምር መስማት ያዳገተ የኦዲዮ ቪዲዮ የምስል ማስረጃዎችን ከተመለከተና ካዳመጠ በኋላ፣ ተከሳሾቹ ላቀረቡዋቸው የሰነድ ማስረጃዎች መግለጫና የክርክር ማቆሚያ ሐሳብ በጽሑፍ ከቀጠሮ በፊት እንዲያቀርቡ፣ ዓቃቤ ሕግም የክርክር ማቆሚያ ሐሳቡን ከቀጠሮ በፊት እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ ተከሳሾች በተጠረጠሩበት የሽብርተኝነት ወንጀል ጥፋተኛ ናቸው ወይም አይደሉም የሚለውን ፍርድ ለመስጠት ለታህሣሥ 11 ቀን 2004 .. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

No comments:

Post a Comment