Wednesday, December 7, 2011

ጉባዔተኞቹ የኤድስ ፈንድ የት እንደገባ በሰላማዊ ሠልፍ ጠየቁ

አካል ጉዳተኞች ቅሬታ አሰሙ

ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ተውጣጥተው በሚሌኒየም አዳራሽ እየተካሄደ ባለው የኤችአይቪ/ኤድስና የአባለዘር በሽታዎች ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ በአፍሪካ (አይካሳ) ጉባዔ ላይ የሚሳተፉ በርካታ ሴቶች፣ በአፍሪካ ለኤችአይቪ/ኤድስ መቆጣጠሪያና መከላከያ ፕሮግራም እንዲውል ከልዩ ልዩ የዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች የተሰጠው ገንዘብ የት እንደደረሰና ምን ላይ እንደዋለ ኅዳር 25 ቀን 2004 .. ባካሄዱት ሰላማዊ ሠልፍ ጠየቁ፡፡ ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸውና ከቫይረሱ ነፃ የሆኑ እነዚሁ ሠልፈኞች ይህንኑ ጥያቄያቸውን ያስተጋቡበትን ሠላማዊ ሠልፍ ያካሄዱት ጉባዔው በሚካሄድበት ቅጥር ግቢ፣ ልዩ ልዩ ፖስተሮች በተለጠፉበትና ኤግዚቢሽኖች በሚካሄዱበት አዳራሽ በመዘዋወር ነው፡፡ በዚሁ ጊዜ ሠልፈኞቹ ‹‹ለኤችአይቪ/ኤድስ ፕሮግራም የተመደበው ገንዘብ የት ደረሰ?›› እያሉ በከፍተኛ ድምፅ ጠይቀዋል፡፡ አንዳንድ የአፍሪካ አገሮች በጀታቸውን ለጄትና ለሌሎች የጦር መሣርያዎች መግዢያ ከሚያውሉት ይልቅ፣ ለዚህ ዓይነቱ ፕሮግራም ስኬታማነት ቢያውሉት ጠቃሚ መሆኑን በአስተያየታቸው ላይ አንፀባርቀዋል፡፡

ሚስ ለይነት ማቦቲ የአፍሪካ አድቮከሲ ቲም መሪና የኤድስ ኤንድ ራይትስ አሊያንስ ፎር ሳውዘርን አፍሪካ በተለይ ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹ይህ ዓይነቱ ዘመቻ መካሄድ የጀመረው 2001 .. ጀምሮ ነው፡፡ በዚህም ብቻ ሳንገታ የአፍሪካ ኅብረትንና የአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን በጽሑፍ ጠይቀናል፤›› ብለዋል፡፡ 

በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ተውጣጥተው በዚሁ ጉባዔ ላይ ተሳታፊ የሆኑ አካል ጉዳተኞች፣ ጉባዔው ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች መብት ጥበቃ ስምምነትን ባከበረ ሁኔታ ባለመዘጋጀቱ የተነሳ ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስትርና የጉባዔው ፕሬዚዳንት ደግሞ ለአካል ጉዳተኞች የተለየ ትኩረትና ቅድሚያ መሰጠቱንና ሊሟሉላቸው የሚያስፈልጉ ልዩ ልዩ ጉዳዮች ሁሉ በጥሩ ሁኔታ እንደተዘጋጀላቸው ገልጸዋል፡፡

አካል ጉዳተኞቹ በተለይ ለሪፖርተር ኅዳር 25 ቀን 2004 .. እንዳመለከቱት፣ ጉባዔው ዓለም አቀፍ ስምምነትን በጣሰ ሁኔታ ለመዘጋጀቱ ከሚያረጋግጡ በርካታ ነጥቦች መካከል አንደኛው፣ በሚሌኒየም አዳራሽ ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኙ መንገዶችና የተዘጋጁት የስብሰባ አዳራሾች በዊልቸርና በአካል ድጋፍ ለሚንቀሳቀሱ አካል ጉዳተኞች ምቹ አለመሆናቸው ይገኝበታል፡፡

ከዚህም ሌላ በሚሌኒየም አዳራሽ ቅጥር ግቢ በተዘጋጀው የማኅበረሰብ መንደር (ኮሚዩኒቲ ቪሌጅ) ውስጥ የተዘጋጀላቸው ፓቫሊዮን (ማሳያ ቦታ) እጅግ በጣም ጠባብ መሆንና በዚህም የተነሳ ምንም ዓይነት መልዕክት ለማስተላለፍ እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡ ይህ ሁሉ ችግር ሊከሰት የቻለው ጉባዔው ገና ከጅምሩ አካል ጉዳተኞችን በሚመለከት በተወያዩበትና ዝግጅት ባካሄዱበት ወቅት አካል ጉዳተኞችን ባሳተፈ መንገድ ባለመሆኑ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል ሚሲዝ ራኬል ካቻጄ የአፍሪካ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ተወካይና ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ምክትል ሊቀመንበር፣ እንደማንኛውም ሰው አካል ጉዳተኞች በኤችአይቪ/ኤድስ እንደሚያዙ ወይም እንደሚጠቁ እየታወቀ በጉባዔው ላይ ግን ይህንን አስመልክቶ የተዘጋጀ ምንም ዓይነት መረጃ እንደሌለ ገልጸዋል፡፡

ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባላድርሻ አካላትና ባለሥልጣናት በተገኙበት በአካል ጉዳተኛ ችግሮችና ጉዳዮች ዙሪያ በሰፊው ውይይት ተደርጎ አንድ ድምዳሜ ላይ ይደረሳል የሚል ተስፋ እንደነበራቸው፣ ነገር ግን የተሰጣቸው ፓቫሊዮን በጣም ጠባብ በመሆኑ የተነሳ እርስ በርሳቸው ብቻ ተነጋግረው ለመለያየት መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህም በአካል ጉዳተኛው ላይ ልዩነት ወይም መድልኦ መድረጉን እንደሚያሳይ አስረድተዋል፡፡ ወደፊት ምን ለማድረግ አስባችኋል? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹በግቢው ውስጠ ሰላማዊ ሠልፍ በማካሄድ ድምፃችን እንዲሰማ እናደርጋለን፤›› ሲሉ ማላዊቷ ሚስዝ ካቻጄ መልሰዋል፡፡

ስማቸው እንዲገለጽባቸው ያልፈለጉ የላይፍ ፎር ወርልድ ባልደረባ፣ ‹‹ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ እነዚሁ አካል ጉዳተኞች በጉባዔው ላይ ሊሳተፉ የቻሉት በሃንዲካፕ ኢንተርናሽናል አማካይነት እንጂ ከጉባዔው አዘጋጆች ጥሪ ደርሷቸው አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ በአካል ጉዳተኞች መካከል የኤችአይቪ/ኤድስ ሥርጭትና የሴት አካል ጉዳተኞች መደፈርም እየተስፋፋ መምጣቱን ባልደረባው ገልጸዋል፡፡ በዚህ ዓይነቱ ችግሮች ዙሪያ አካል ጉዳተኛውን ሳያሳትፍ የሚደረግ ውይይት ፍሬ አልባ እንደሚሆንና ይህም ለአካል ጉዳተኞች በቂ ትኩረት አለመሰጠቱን እንደሚያመላክት ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሃንዲካፕ ኢንተርናሽናል ተወካይ፣ በአዳራሹ እንዲሰጣቸው ያመለከቱት 25 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ፓቫሊዮን እንደነበር፣ እስከ ኅዳር 24 ቀን 2005 ድረስ በጠየቁት መሠረት እንደሚሰጣቸው ሲነገራቸው ቆይቶ ኅዳር 25 ቀን 2004 .. ዘጠኝ ካሬ ሜትር የምትሆን ቦታ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ወንበርና ጠረጴዛ እንደሌላቸውና በዚህ በተጣበበ ሁኔታ ምን ዓይነት ሥራ ለማከናወን አልቻልንም ብለዋል፡፡

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖምና የኤችአይቪ ኤድስና የአባላዘር በሽታዎች ዓለም አቀፍ ጉባዔ ፕሬዚዳንት ዶክተር ይገረሙ አበበን ሪፖርተር ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ አነጋግሮአቸዋል፡፡ ዶክተር ይገረሙ እንዳብራሩት ከሆነ፣ ከጉባዔው ቅድመ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ጉባዔው ወቅት ድረስ በተከናወነው እንቅስቃሴ ላይ ሃንዲካፕ ኢንተርናሽናል አካል ጉዳተኞችን ወክሎ ተሳትፏል፡፡

ከዚህም ሌላ እያንዳንዱ ጉባዔተኛ 400 ዶላር በላይ እየከፈለ እንዲሳተፍ ሲደረግ አካል ጉዳተኞችና ረዳቶቻቸው ግን ከክፍያ ነፃ ሆነው እንዲሳተፉ መደረጉን፣ የተለየ የንጽህና መጠበቂያ (መፀዳጃ ሥፍራ) እንደተዘጋጀላቸውና ለዚህም የሚሆን ማቴሪያል ከአገር ውስጥ ገበያ ለማግኘት ባለመቻሉ የተነሳ ከዱባይ ተገዝቶ አገልግሎት ላይ እንዲውል መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ዶክተር ቴዎድሮስ፣ ‹‹እስካሁን ድረስ አብረን ስንሠራ ቆይተን አካል ጉዳተኛውን ገለል አድርጋችኋል መባላችን በእጅጉ አሳዝኖኛል፡፡ በአዳራሹ የየራሳቸውን ዝግጅት ለማሳየት የሚያስችላቸው ፓቫሊዮን እንዲሰጣቸው ጥያቄ ያቀረቡ ድርጅቶች ቁጥር እጅግ የበዛና ከአቅም በላይ ሆኖ በመገኘቱ የተነሳ፣ ለማብቃቃት ሲባል ፓቫሊዮኖችን ጠበብ ለማድረግ ተገድደናል፤›› ብለዋል፡፡

http://ethiopianreporter.com/

No comments:

Post a Comment