Wednesday, November 9, 2011

በፑንትላንድ ከሞት የተረፈው ኢትዮጵያዊ እስካሁን አልተፈታም::እህቱ በባህሉ መሠረት ለጋብቻ ተጠይቃለች

ከሶማሊያ ተገንጥላ ራሷን በምታስተዳድረው ፑንትላንድ ቦሳሶ ከተማ ውስጥ የሞት ፍርድ ተፈርዶበት በድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) የገንዘብ ልገሳ የተረፈው ኢትዮጵያዊው አስመሮም ኃይለ ሥላሴ፣ እስካሁን ድረስ አለመፈታቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ግለሰቡ ከዓመት በፊት በሰው መግደል ወንጀል በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ ዕርምጃ እንዳይወሰድበት የኢትዮጵያ መንግሥት ባደረገው ከፍተኛ ጥረት ሊተርፍ ችሏል፡፡

 ፑንትላንድ አስተዳደር ውስጥ ያለው የኢትዮጵያ ቆንስላ፣ የአስተዳድሩን ፕሬዚዳንት አግኝቶ እንዳነጋገረ የገለጹት ቃል አቀባዩ፣ የአካባቢው ጐሳ መሪዎች ጉዳዩን በሰላምና በእርቅ ለመጨረስ ሦስት ጥያቄዎችን ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡

 የጎሳ መሪዎቹ ያቀረቧቸው ጥያቄዎች አስመሮም ገደለው ለተባለው ግለሰብ ቤተሰቦች ጠመንጃ ገዝተው መስጠት እንዳለባቸው፣ የእሱ እህት ወይም ዘመድ በባህላቸው መሠረት የሆነች ልጅ ለሟች ዘመድ እንድትዳርላቸውና 700 ሺሕ ብር የደም ካሳ እንዲከፈላቸው መጠየቃቸውን አምባሳደር ዲና ጠቁመዋል፡፡

 የኢትዮጵያ ቆንስላ በአስመሮም ላይ ግድያው እንዳይፈጸም በሚያደርገው ጥረት፣ አንድ ጊዜ የገዳይ እናት ሌላ ጊዜ አባቱ ሲጠፉ፣ እነሱ ሲገኙ ደግሞ ያገባናል የሚሉ የጐሳ ሽማግሌዎች ሲባል መፈታቱ እስካሁን እየተጓተተ መሆኑን ቃለ አቀባዩ አስረድተዋል፡፡

 ኢትዮጵያዊው ስደተኛ መሆኑንና የጠየቁት ጥያቄ ደግሞ በኢትዮጵያ ባህል ነውር መሆኑን በመግለጽ፣ የኢትዮጵያ ቆንስላ በፑንትላንድ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከሟች ወላጆች፣ ከአገሩ ዓቃቤ ሕግና ከፍርድ ቤት ጋር እየተነጋገረ መሆኑን፣ ምንም ይሁን ምንም የሞት ፍርዱ ተፈጻሚ እንደማይሆንና እንደሚለቀቅ አምባሳደር ዲና አረጋግጠዋል፡፡

 ‹‹በፑንትላንድ ሞት የተፈረደበት ኢትዮጵያዊ ቤተሰቦች መንግሥትን እየተማፀኑ ነው›› በሚል ጥቅምት 15 ቀን 2004 ዓ.ም. ሪፖርተር የዘገበውን ዜና በማንበብ፣ ግለሰቡ የተጠየቀውን 700 ሺሕ ብር የነፍስ ዋጋ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን ‹‹ቴዲ አፍሮ›› በመክፈል ከሞት ማትረፉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
 http://ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment