Wednesday, October 26, 2011

በፑንትላንድ ሞት የተፈረደበት ኢትዮጵያዊ ቤተሰቦች መንግሥትን እየተማፀኑ ነው

•    ከሞት ለመትረፍ እስከ ዓርብ 700 ሺሕ ብር መክፈል አለበት

ከሶማሊያ ተገንጥላ ራሷን በምታስተዳድረው ፑንትላንድ ውስጥ በምትገኘው ቦሳሶ ከተማ የሞት ፍርድ የተፈረደበትን ኢትዮጵያዊ ቤተሰቦች፣ መንግሥት እንዲያተርፍላቸው እየተማፀኑ ነው፡፡ በሰው መግደል ወንጀል ተከሶ ባለፈው ሳምንት በሞት እንዲቀጣ በከተማዋ የጎሳ አባላት ውሳኔ የተላለፈበት ኢትዮጵያዊው አስመሮም ኃይለ ሥላሴ፣ የፊታችን ዓርብ ድርስ 700 ሺሕ ብር መክፈል ከቻለ ከመገደል እንደሚተርፍ ቤተሰቦቹ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

እንደ ቤተሰቦቹ ገለጻ፣ አስመሮም ሞት የተፈደበት ሆን ብሎና አስቦ ሰው ገድሎ ሳይሆን፣ በመኖርያ ቤቱ ውስጥ እያለ ባለቤቱን ለመድፈር በመጡ ግለሰቦች ጥቃት ተፈጽሞበትና ጉዳት ደርሶበት ነው፡፡ ሕይወቱን ለማትረፍ ባደረገው የአልሞት ባይ ተጋዳይነት የአንዱ ግለሰብ ሕይወት አልፏል ይላሉ፡፡

ቤተሰቦቹ ስለጉዳዩ በተደጋጋሚ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በደብዳቤ ቢያሳውቁም፣ በቂ ምላሽ አለማግኘታቸውን ገልጸው፣ ምናልባት በሥራ መደራረብና የባሱ ጉዳዮችን ከመፈጸም አኳያ፣ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ድርጊቱን ያልሰሙ ከሆነ፣ ‹‹ሁለት ቀን ብቻ›› የቀረውን ልጃቸውን እንዲያተርፉላቸው ተማፅነዋል፡፡

መንግሥት በተለያዩ አገር ለሚኖሩ ዜጐቹ የሚያደርገውንና የሚሰጠውን የተቆርቋሪነት ስሜት፣ ለልጃቸውም እንደሚያደርገው ጥርጥር እንደሌላቸው የገለጹት ቤተሰቦቹ፣ ለጊዜው አቅማቸው ሊከፍለው ያልቻለውን የልጃቸውን ነፍስ ማትረፊያ ገንዘብ ከፍሎ ቢያድንላቸው፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመክፈል የሚችሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሞት ፍርዱ ሊፈጸምበት ሁለት ቀናት ብቻ የቀሩት የአስመሮም ኃይለ ሥላሴ ቤተሰቦች ያቀረቡትን ተማፅኖ በሚመለከት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጄነራል ዳይሬክቶሬት ዴስክ ኃላፊ አቶ መላኩ ዲዳን አነጋግረናቸው፣ ‹‹በየትኛውም አገር በዜጐች ላይ ችግሮች ሲኖሩ ክትትል የማድረግ ሥራ እንሠራለን፡፡ እነሱም አመልክተው ከሆነ ማመልከቻቸውን መሠረት አድርገን በሚሲዮኖቻችን አማካይነት አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል፡፡ ክትትል እናደርግላቸዋለን፡፡ ይኼንን አድርገናል፤›› ካሉ በኋላ ዝርዝር ማብራሪያ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡

ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባልደረባ እንደገለጹት፣ የልጁ ቤተሰቦች ተደጋጋሚ ማመልከቻ አቅርበዋል፡፡ በሰው መግደል ወንጀል ሞት እንደተፈረደበትም ይታወቃል፡፡ እንዲከፍል የተጠየቀው 700 ሺሕ ብርም ትክክል ነው፡፡ በሶማሊያ ሰው የገደለ የነፍስ ዋጋ ከከፈለ አይገደልም፡፡ በእሱም ላይ የሆነው ይኼው ነው፡፡ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ አሥር ቀናት ቢሰጠውም፣ መንግሥት ግን ምን እንደሚወስን አልታወቀም ብለዋል፡፡

No comments:

Post a Comment