Sunday, October 9, 2011

መምርያው የናይጄሪያን አውሮፕላን በ80 ሺሕ ብር መነሻ ለጨረታ አቀረበ


የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አፈጻጸም መምርያ ተሸጦ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲከፈል ተወስኖበት የነበረውንና ንብረትነቱ የናይጄሪያው ትራንስሳሀራን አየር መንገድ የሆነውን አውሮፕላን፣ መስከረም 30 ቀን 2004 ዓ.ም በሐራጅ በ80 ሺሕ ብር መነሻ ዋጋ እንዲሸጥ ለጨረታ አቀረበው፡፡.
መምርያው ግንቦት 29 ቀን 2003 ዓ.ም. በአውሮፕላኑ ላይ ያካሄደው ግምገማ እንደሚያሳየው፣ የቀለም ቅብ የሚያስፈልገው፣ ወንበሮቹ የተፈታቱና ሞተሮቹም የተገነጣጠሉ በመሆናቸው ለማንቀሳቀስ አመቺ አይደሉም፡፡ አውሮፕላኑ አሁን ባለው ይዞታ ለአገልግሎት ዝግጁ አይደለም፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጳጉሜን 2003 ዓ.ም. በጻፈው የግምት ማሳወቂያ ደብዳቤ መሠረት፣ የአውሮፕላኑ ጨረታ መነሻ ዋጋ 80 ሺሕ ብር መሆኑን አስታውቋል፡፡ ይህንንም የመነሻ ዋጋ ሊያቀርብ የቻለው በሚያዝያ 2000 ዓ.ም. ሌላ አውሮፕላን በተመሳሳይ ዋጋ በመሸጡ መሆኑን በደብዳቤው ላይ ገልጿል፡፡

አውሮፕላኑ ለጨረታ የቀረበው ትራንስሳሀራን አየር መንገድ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ አንድ አውሮፕላን እንዲጠገንለት ከሰጠ በኋላ፣ የተዋዋለውን 184,218.76 ዶላር የመጠገኛ ዋጋ መክፈል ባለመቻሉ፣ ሊከፈለኝ ይገባል በማለት ታኅሣሥ 18 ቀን 1999 ዓ.ም. ክስ ከመሠረተ በኋላ ነው፡፡

ክሱ የቀረበለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስምንተኛ ፍትሐ ብሔር ልደታ ምድብ ችሎትም የካቲት 26 ቀን 2000 ዓ.ም. በሰጠው ውሳኔ፣ የናይጄሪያው አየር መንገድ የተባለውን ገንዘብ እንዲከፍል ፈርዶበታል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድም የፍርድ ቤቱን ውሳኔ መሠረት በማድረግ የአፈጻጸም ማመልከቻ ያስገባ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱም ትራንስሳሀራን አየር መንገድ 3.9 ሚሊዮን ብር እንዲከፍል፣ ይህ ካልሆነም በኢትዮጵያ አየር መንገድ እጅ የሚገኘው አውሮፕላን ተሸጦ እንዲከፈል በማለት ትዕዛዝ ማስተላለፉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment