Wednesday, August 3, 2011

መድረክ የሰላማዊ ሠልፍ ጥሪውን ውድቅ አደረገው
WEDNESDAY, 03 AUGUST 2011 09:29

‹‹ማንም ተሳተፈም አልተሳተፈ ሠልፉ አይቀርም›› የኢትዮጵያ አንድነት ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኢአዴድ)

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ሁለት የተቃዋሚ ፓርቲዎች በመስቀል አደባባይ ሕዝባዊ የተቃውሞ ሠልፍ በጋራ ለመጥራት ያቀረቡለትን ጥሪ አለመቀበሉን ለሪፖርተር አስታወቀ፡፡ የመላው ኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲና (መኢዴፓ) የኢትዮጵያ አንድነት ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኢአዴድ) በጋራ የጠሩትን የትብብር ጥሪ ያልተቀበሉበትን ምክንያት የመድረክ ሊቀመንበር ዶክተር ሞጋ ሶሬሳ አስረድተዋል፡፡ ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ ብዙ የቤት ሥራ መሠራት አለበት፡፡ ምንም ዓይነት ዝግጅት ሳይደረግ የተቃውሞ ሠልፍ መጥራት የራሱ አደጋ አለው፡፡ መድረክ ገና በመደራጀት ላይ ነው፤ ስለዚህ ዝም ብሎ የተጠየቀውን መቀበል ግብታዊ መሆን ነው ብለዋል፡፡

‹‹የሁለቱን ፓርቲዎች ሐሳብ እናደንቃለን፣ እንደግፋለን፣ ስለጥሪውም እናመሰግናለን፤›› ያሉት ዶክተር ሞጋ፣ ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ ሊፈጠሩ የሚችሉ አደጋዎች ይኖራሉ ይላሉ፡፡ ‹‹በሠልፉ መሀል ጣልቃ በመግባት ሌላ ዓላማ ሊያራምድ የሚፈልግ አካል ቢኖር በምን መልኩ መከልከልና መቋቋም እንደሚቻል ራሱን የቻለ ጥናት ስለሚያስፈልገው፣ መድረክ የራሱን ጊዜ ወስዶ ማጥናትና መዘጋጀት ያስፈልገዋል፤›› በማለት የሰላማዊ ሠልፉን ጥሪ ውድቅ ያደረጉበትን ምክንያት ተናግረዋል፡፡

ሁለቱ ፓርቲዎች ሕዝባዊ የተቃውሞ ሠልፍ ለማድረግ የተነሱባቸውን ነጥቦች መድረክ በተለያዩ ስብሰባዎቹና መግለጫዎቹ ለኅብረተሰቡ ያስተላለፋቸው በመሆናቸው ብዙም አዲስ ነገር እንደሌለበት ሊቀመንበሩ አስታውሰዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የመድረክ አባል ፓርቲዎች ሐምሌ 25 ቀን 2003 ዓ.ም ተሰባስበው የጋራ ውሳኔ ላይ መድረሳቸውንም አስረድተዋል፡፡
‹‹እኛ ጥሪ ያደረግንላቸው ነገ ተነስተን ሕዝባዊ የተቃውሞ ሠልፍ እናድርግ ሳይሆን፣ አምባገነኑ የኢሕአዴግ መንግሥት በሕዝቡ ላይ እያደረሳቸው ባሉ የተለያዩ በደሎች ላይ ተወያይተን ሰላማዊ ሠልፍ እናድርግ ነው፤›› ያሉት የኢትዮጵያ አንድነት ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኢአዴድ) ፕሬዚዳንት አቶ አድማሱ ኃይሉ ናቸው፡፡
እንደ አቶ አድማሱ ገለጻ፣ ማንም ፓርቲ ተሳተፈም አልተሳተፈም ሕዝባዊ የተቃውሞ ሠልፍ አዲሱ ዓመት ከመግባቱ በፊት በመስቀል አደባባይ ይደረጋል፡፡ የመላው አማራ ድርጅት (መአድ) ለዛሬ በጠሩት ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ሆኗል፡፡ አስፈላጊውን ምክክርና ውይይት ካደረጉ በኋላ ባነሷቸው ሰባት ነጥቦች ላይ ሰላማዊ ሠልፉን ለማካሄድ ከሚመለከተው አካል ፈቃድ እንደሚጠይቁ አስታውቀዋል፡፡
ሁለቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በመስቀል አደባባይ ሕዝባዊ የተቃውሞ ሠልፍ የሚያደርጉባቸው ዋና ዋና ነጥቦች ሚሊዮኖች በችግር፣ በፍትሕ እጦትና በረሀብ (ድርቅ) ሰለባ በኑሮ ውድነቱ፣ እየተጣለ ባለው ገደብ ያጣ የግብርና የታክስ አወሳሰንና ሊከተል በሚችለው የዋጋ ንረት፣ የኢሕአዴግ መንግሥት የነፃውን ፕሬስና የሕዝቡን ጥያቄ ለማፈንና ለማሸማቀቅ ያወጣውን የሽብርተኝነት ሕግና ተግባራዊነቱን በሚመለከት፣ ግልጽ ባልሆነና ባልታወቀ ሁኔታ ለውጭ አገር ዜጎች ለ99 ዓመታት በሊዝ እየተሰጠ ስላለው የአገሪቱ ለም መሬት ጉዳይ፣ በመዋቅር ማሻሻያ ስም ሠራተኞች ከሕግ አግባብ ውጭ ከሥራ የማሰናበትና ማፈናቀል፣ የትምህርት ጥራት ጉድለትና ሌሎችንም በተመለከተ መሆኑን በጋራ ባወጡት የጥሪ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

No comments:

Post a Comment